NEWS: የደመራ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ ይከበራል

                                                  

የመስቀል ደመራ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማንያን ደመራ በመደመር በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ያከብሩታል።

በተለይም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚከበረው የደመራ በዓል ላይ የሃይማኖቱ መሪዎችና ተከታዮች እንዲሁም የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን አማካይነት የተለያዩ ዝማሬዎችም ይቀርባሉ።

ይህንን ሃይማኖታዊ በዓል ለመታደም የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ቅዱስ ባስልዮስ ትላንት አዲስ አበባ ገብተዋል።

ፓትርያሪኩ በበዓሉ ለመታደም የመጡት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ግብዣ ነው።

በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በበዓሉ ወቅት ከፍተኛ ድምጽ የሚያወጡ፣ ህብረተሰቡን የሚያውኩና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተከለከሉ ርችቶችን መጠቀም የተከለከለ መሆኑን እና በህግ እንደሚያስጠይቅ ነው ኮሚሽኑ ያሳሰበው።

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠርና መከላከል ባለስልጣን በበኩሉ፥ ህብረተሰቡ የመስቀል ደመራ በዓልን ሲያከብር የእሳት አደጋ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

ህብረተሰቡ ለበዓሉ ደመራ ሲያቆም ከኤሌክትሪክ መስመሮች የራቁ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ባለስልጣኑ አሳስቧል።

የመስቀል በዓልን ለማክበር በሚከናወነው የደመራ ማቆምና ማብራት ስነ ስርአት ሲከናወን፥ እሳት አደጋ ከሚያስከትሉ ሁኔታዎች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ነው የገለፀው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement