1 ኪሎ ግራም ወርቅ በአንጀቱ የደበቀው ስሪ ላንካዊ በቁጥጥር ስር ዋለ

                                                                     

ስሪ ላንካ 1 ኪሎ ግራም የሚመዝን ወርቅና ጌጣጌጦችን በአንጀቱ ውስጥ ደብቆ ወደ ሌላ ሀገር ለመውሰድ የሞከረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አዋለች።

የሀገሪቱ የጉምሩክ ተቆጠጣሪዎች 4 ነጥብ 5 ሚሊየን የስሪ ላንካ ሩፒ ወይም 29 ሺህ 370 የአሜሪካ ዶላር የሚገመት 904 ግራም ወርቅ ነው በግለሰቡ አንጀት ውስጥ ያገኙት።

የ45 ዓመቱ ጎልማሳ ወርቅ እና ጌጣጌጡን በሆዱ ውስጥ ይዞ ወደ ህንድ ሲጓዝ፥ በኮሎምቦ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ተይዟል።

በአውሮፕላን ማረፊያው የነበሩ የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ሰራተኞች “ግለሰቡ በሚያስጠረጥር መልኩ ሲራመድ ስለነበረ ነው በቁጥጥር ስር ያዋልነው” ብለዋል።

እንድተያዘም በመሳሪያ በተደረገ ፍተሻ በአንጀቱ ውስጥ በማይበሰብሱ ቦርሳዎች ወርቁን እና ጌጣጌጡን መያዙ መረጋገጡን ተናግረዋል።

በውስጡም አራት ባለጠርዝ የወርቅ ስሪቶች፣ ሶስት የወርቅ ስብርባሪዎች፣ ስድስት ከወርቅ የተሰሩ ጌጣጌጦች እና ከወርቅ እና ከብር ተቀላቅለው የተሰሩ ሁለት ጌጣጌጦች መገኘታቸውን የጉምሩክ ተቆጣጣሪ መስሪያቤቱ ቃል አቀባይ ገልፀዋል።

በሀገሪቱ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጉዳዮች መከሰታቸው ተገልጿል።

ወርቅ በሰውነታቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የሚያዘዋውሩ ወንጀለኞች ወርቁን የሚገዙት፥ በርካሽ ዋጋ ከሚሸጥባቸው እንደ ዱባይ እና ሲንጋፖር ካሉ ከተሞች ነው።

ወደ ህንድ የሚያሸጋግሩትም ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝላቸውን ሽያጭ ስለሚያከናውኑ ነው ተብሏል።

ባሳለፍነው ሳምንት አንድ ስሪ ላንካዊት 314 ነጥብ 5 ግራም የሚመዝን ወርቅ በተመሳሳይ ሁኔታ በአንጀቷ ደብቃ ወደ ህንድ ስታመራ በቁጥጥር ስር መዋሏ ይታወሳል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement