NEWS: ቅዱስ ጊዮርጊስ የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚን እንዲያስተዳድር ከስፔኑ ሶክስና ጋር ተፈራረመ

                                           
ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም የተመረቀምው የይድነቃቸው ተሰማ ስፖርት አካዳሚን እንዲያስተዳድር ከስፔኑ ሶክስና ጋር ተፈራረመ።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ከሶክስና የእግር ኳስ ማዕከል እና ኢ ፎር ኢ ጋር በትናንትናው እለት የተፈራረመው ስምምነትም ለ5 ዓመት የሚቆይ መሆኑ ተነግሯል።

በፊርማው ስነ ስርዓት የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ ፕሬዝደንት አቶ አብነት ገብረመስቀል፥ የእግርኳስ አካዳሚ መገንባት የክለባቸው የረጅም ግዜ ምኞት እንደነበር ገልፀዋል። 

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሶክስና ስምምነት ለኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች ወሳኝ የሆነ ኢንቨስትመንት ነው ያሉት አቶ አብነት፥ በስፔን እና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነትም የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

የሶክስና የእግርኳስ ማዕከል ምክትል ፕሬዝደንት ዴቪድ ሎፔዝ በበኩላቸው፥ ድርጅታችን በታዳጊዎች ስልጠና ፕሮግራሞች ላይ በልዩነት የሚሰራ ነው፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ መመረጥ መቻላችን ትልቅ ክብር ነው ብለዋል። 

የሶክስና የእግርኳስ ማዕከል የመጀመሪያ ስራ ተስጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች ጋር በመሆን የመለየት ስራ ነው ሲሉም ተናግረዋል። 

ለቅዱስ ጊዮርጊስ አካዳሚ የሚሆን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እንደሚቀርጹም አስታውቀዋል።

በስፔን፣ ቻይና እና ሆንግ ኮንግ ቢሮዎች አሉን ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ በቅርቡ በኢትዮጵያም ይኖረናል ማለታቸውን ከሶከር ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

ሶክስና በስፔን ማድሪድ፣ በቻይና ጉዋንዡ ግዛት እና በሆንግኮንግ ማዕከላት ያሉት ሲሆን፥ በሁለቱ ሀገራት ከተሞች ከሚገኙት ሪያል ማድሪድና ጉዋንዡ ኤቨርግራንዴ የታዳጊ ወጣቶች ማሰልጠኛ ከፍቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

በመጋቢት 2009 የተመረቀው የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ 50 ለሚሆኑ ታዳጊዎች ስልጠናውን በመስጠት ወደ ስራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement