NEWS: 16 ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሕጉ ላይ ድርድር ጀመሩ

                                                               

በበላይ ተስፋየ

16 ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሕጉ የማሻሻያ ሀሳቦች ላይ ድርድር ጀመሩ።

የፖለቲካ ፓርቲ በተመጣጣኝ ድምፅ የፓርላማ ወንበር የሚያገኙበት ስርዓት እንዲኖር እንደሚፈልጉ፥ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቡት የድርድር ፅሁፍ ላይ ጠቅሰዋል።

የኢህአዴግ ተደራዳሪዎች አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ እና አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በምርጫ ሕጉ 532/1999 የተዘጋጀውን የምርጫ ፅሁፍ አቅርበዋል።

በምርጫ ሕጉ መሰረት አሁን አብላጫ ድምፅ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ በክልልም ይሁን በፌደራል የመንግስት ምክር ቤቶች መቀመጫ የሚይዝ ይሆናል ተብሏል።

ይህ አሰራር በዓለም አቀፍ ደረጃ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል የተመረጠ እና ውጤታማ አሰራር መሆኑን አቶ አስመላሽ ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ አምስት ምርጫዎች በተከታታት በዚህ መንገድ የተካሄዱ ሲሆን፥ ስርዓቱም በራስ ዴሞክራሲ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳለ እና ዴሞክራሲ በማሳደግ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ መሆኑ ተገልጿል።

ሆኖም የብዙሃን የመወሰን መብት ለማስከበር የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመደመጥ መብት በማከል የዴሞክራሲ ስርዓትን የበለጠ ለማስፋት የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚካተቱበት ስርዓት መዘርጋት ያሻል ተብሏል።

ኢህአዴግ በምርጫ ሕጉ የአብላጫ ድምፅ እና ተመጣጣኝ ቅይጥ የያዘ የምርጫ ስርዓት በምርጫ ሕጉ እንዲካተት በድርድሩ አቅርቧል።

ይህ ስርዓትም በክልል እና በፌደራል መንግስት ምክር ቤቶች ብቻ ተግባራዊ እንዲደረግ እንደሚፈልግ ነው የተገለፀው።

የአብላጫ ድምፅ ስርዓቱ በዋናነት ተግባራዊ የሚያደረግ ሲሆን፥ አቶ አስመላሽ እንደገለፁት ከሆነ ውህዳን (ማይኖሪቲ) በፓርላማ መቀመጫ የሚያገኙበት ስርዓት የሚኖር ይሆናል።

ይህ ስርዓት ደግሞ በድርድር ሂደት የሚወሰን ሲሆን አሁን ካሉ የፓርላማ መቀመጫ የተወሰኑት ድርሻ በድርድሩ መጨረሻ እንደሚታወቅ ተጠቁሟል።

በዚህ መሰረት ተመጣጣኝ ድምፅ ያገኙ ፓርቲዎች ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ 23 መቀመጫዎች በፓርላማ ውስጥ አሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ 18 በአብላጫ ድምፅ የሚያዙ ከሆነ አምስቱ ደግሞ በተመጣጣኝ ድምፅ የሚያዙበት ስርዓት እንደሚሆን በአብነት በማንሳት ተብራርቷል።

በዚህ አሰራር መሰረትም አሁን ካሉት መቀመጫዎች በተጨማሪ ፓርላማው ተጨማሪ ቁጥር እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑ በዝርዝር ተገልጿል።

አተገባበሩ በ12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የመደራደሪያ ፅሁፉ ላይ በኢዴፓ ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በኩል ቀርቧል።

በዚህ መሰረት ተመጣጣኝ ውክልና በቀጥታ ተግባራዊ እንዲደረግ ለድርድር አቅርበዋል።

በዚህም መሰረት በአንድ የምርጫ ክልል የሚሰጠውን ድምፅ ለክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ በማካፈል የሚገኘው ቁጥር ወንበር ለማገኘት መነሻ ሆኖ እንዲያገለግል ነው በፓርቲዎቹ የቀረበው።

ከመነሻ የድምፅ ቁጥር በላይ የሚኖራቸው ድምፅ እየተሰላ በምክር ቤቱ ያለውን መቀመጫ የሚያገኙበትስርዓት እንዲኖርም ባቀረቡት ፅሁፍ ላይ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በምርጫ ቦርዱ አደረጃጀት ላይ አሁን ገለልተኛ ወይም ነፃ አይደለም የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል።

ስለዚህ አሁን ያለው ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የምርጫ ቦርዱን በበላይነት እንዲመሩትና ከምርጫ ሂደቱ ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ስራውን የሚሰራ የምርጫ ኮመኚሽንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የሚሾም እንዲሆንም በፅሁፉ ቀርቧል።

ምክትሎቹ በሚሾመው ኮሚሽን አማካይነት ለቦርዱ ቀርበው የሚፀድቅ ሲሆን፥ ሌሎቹ ከታችኛው ያሉት የምርጫ ክልል ደግሞ በውድድር የሚሚመደቡበት ስርዓት እንዲኖር እንደሚፈልግ ነው የ12 ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የገለፀው።

 

 

 

 

 

 

Advertisement