NEWS: የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ የተመድ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ እንዲሻሻል ያቀረበችውን የውሳኔ ሀሳብ አፀደቀ

                                                      

የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የተመድ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ ማሻሻያ ሀሳብን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ  ባካሄደው ልዩ ስብሰባው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ አፋጣኝ ማሻሻያ እንዲደረግ የሚጠይቀውን ይህን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ ነው ያፀደቀው።

በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ እንደመሆኗን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስብሰባውን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል።

የተለያዩ አገራት ፕሬዚዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና አምባሳደሮች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።

የማሻሻያ ሀሳቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ስራ ውጤታማ እንዲሆን እንዲሁም ለሰላም ማስከበር የሰላም አስከባሪው ጦር አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ሊሟሉለት እንደሚገባ የሚጠይቅ ነው።

የማሻሻያ ሀሳቡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን መካከልም አጋርነት መኖር እንዳለበት የሚያመላክት ሲሆን፥ በተለይም በፀጥታው ምክር ቤት ስር በአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም አስካባሪ ሀይል በምን መልኩ የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም ይደነግጋል። 

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የውሳኔ ሀሳቡ ከፀደቀ በኋላ እንደተናገሩት፥ የውሳኔ ሀሳቡ መፅደቅ በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺህ በላይ የሰላም አሰከባሪ ሀይል በተለያዩ አከባቢዎች ላሰማራችው ኢትዮጵያ ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የተመድ ሰላም አስከባሪዎች በተሰማሩባቸው አከባቢዎች ያለው ነባራዊ ሁኔታ መቀየሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሰላም አስከባሪዎች ጊዜው የሚጠይቀውን ትጥቅ ባለመታጠቃቸው ሰላምን ማስጠበቅ፣ ሰላማዊ ሰዎችን እና ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እየተሳናቸው መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህም በመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ይህን ችግር ለመፍታት በመሪዎች ደረጃ ስብሰባውን ያካሄደው ምክር ቤቱ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ቃል ገብቶ እንደነበር በንግግራቸው አስታውሰዋል።

የተመድ ዋና ፀሃፊም የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ለማሻሻል የነበራቸውን ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል።

ምክር ቤቱም በውሳኔው ለዋና ፀሃፊው ጥረት ፖለቲካዊ ድጋፍ መስጠቱንም ነው ያነሱት።

ምክር ቤቱ ማሻሻያውንም በተገቢው መልኩ እንዲተገበር እንዲያደርግም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተመድ የሰላም ማስከበር ጥላ ስር በዳርፉር፣ አብዬ እና ደቡብ ሱዳን የሰላም አስከባሪዎችን አሰማርታለች።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement