NEWS: ጠ/ሚ ኃይለማሪያም በክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት እንዲቆም መንግሥት ሕገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ ገለፁ

                                                               

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ አገር ሽማግሌዎችን፣ የሐይማኖት አባቶችንና አባ ገዳዎችን እንዲሁም የሁለትን ክልሎች ርዕሰ መስተዳደርችን አነጋገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግጭቱ ሳቢያ የሰው ህይወት በመጥፋቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለጹ ሲሆን፥ ግጭቱ በአስቿይ እንዲቆም የፌዴራል መንግሥት ሕገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ አፋጣኝ እርምጃዎችን ይወስዳል ብለዋል።
የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ሰላም የማስፋኑ ሂደት ሚናቸውን እንዲወጡም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያደረጉት።

በዚህ መሠረት የአካባቢዎቹን ሰላምና ፀጥታ ወደነበረበት ለመመለስ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ክትትል ሥር እንዲሆኑ፣ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የሕዝቡን ሰላም የመጠበቅና የማረጋጋት ሥራ እንዲሰሩም፣ አካል በማጉደልና የሰው ሕይወት በማጥፋት የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያመ አዘዋል።

ግጭቱ በተከሰተባቸው ድንበር አካባቢዎችና የግጭቱ ቀጠናዎች የፌዴራል መንግሥት ማንኛውንም የጦር መሣሪያ ወይም ትጥቅ የሚያስፈታ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በሁለቱ ክልሎች መካከል የሰብዓዊ መብት በመጣስ የሰው ሕይወት ያጠፋ የፀጥታ ኃይልም ሆነ ማንኛውም አካል በሕግ አግባብ እርምጃ እንዲወሰድበት እንደሚደረግም አስታውቀዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

“የዜጎች ሠላም የማይዋጥላቸው ፀረ-ሠላም ኃይሎች ችግሩ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዲሄድ በማድረጋቸው መንግሥት በሚያደርገው የማጣራት ሥራ ሁሉም ዜጋ ከመንግሥት ጎን በመቆም ትብብር ሊያደርግ ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ሕዝቡን የሚያጋጭ መግለጫ በመስጠት ብጥብጡን በሚያባብሱና ከዚህ እኩይ ተግባራቸው በማይታቀቡት ላይ “መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል” ብለዋል።

ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መበት ጥሰትን እንደሚያጣራም ነው ያስታወቁት።

በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት የሚያባብሱ የመገናኛ ብዙኃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ይህ የማይሆን ከሆነ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አሳስበዋል።

በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ የትኛውም ግለሰብና የፀጥታ ኃይልም ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement