NEWS: ሰሜን ኮሪያ በሳምንታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የባለስቲክ ሚሳኤል ወደ ጃፓን አስወነጨፈች

                                           

ሰሜን ኮሪያ በሳምንታት ውስጥ ሁለተኛ የሆነውን ጃፓንን ያቋረጠ የባለስቲክ ሚሳኤል አስወነጨፈች።

የደቡብ ኮሪያ ጦር እንዳስታወቀው የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል 770 ኪሎ ሜትር ወደ ላይ የተወነጨፈ ሲሆን፥ ሚሳኤሉ ሆካይዶ ባህር ወስጥ ከመውደቁ በፊት 3 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ተጉዟል።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፥ አገራቸው እንዲህ ዓይነቱን የፀብ ጫሪ ድርጊት ፈፅሞ አትታገስም ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያ ይህን አካሄዷን ከቀጠለች መጪ ተስፋዋ ደህና አይሆንም ሲሉም ተናግረዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰንም በሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ዙሪያ አስተያይት የሰጡ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጣለውን ማእቀብ የጣሰ ነው ብለዋል።

የሰሜን ኮሪያ የንግድ አጋር የሆኑት ቻይና እና ሩሲያም ሰሜን ኮሪያን ከዚህ ተግባር ማስቆም አለባቸው ሲሉ ሀላፊነቱን ሰጥተዋቸዋል።

ቻይና ለሰሜን ኮሪያ አብዛኛውን የነዳጅ ፍጆታ ታቀርባለች፤ ሩሲያ ደግሞ በርካታ የሰሜን ኮሪያ የሰው ሀይልን ቀጥራ ታሰራለች ሲሉም ሬክስ ቲለስረን ተናግረዋል።

ቻይና እና ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ ጠብ አጫሪ የሚሳኤል ማስወንጨፍ ተግባር ዙሪያ የራሳቸውን እርምጃ በመውሰድ ሀገሪቱን እንደማይታገሷት ማሳየት አለባቸውም ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያ የባላስቲክ ሚሳኤል መተኮሷን ተከትሎ ከደቂቃዎች በኋላ ደቡብ ኮሪያም ሁለት የባላስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ባህር መተኮሷ ተነግሯል።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄይኢን የሀገሪቱን የፀጥታ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውም ተነግሯል።

በስብሰባቸውም ሰሜን ኮሪያ ፀብ አጫሪ ተግባሯን ከቀጠለች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢኮኖሚያዊ እና የዲፕሎማሲያዊ መገለል ሊደርስባት አንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ሰሜን ኮሪያ ከሁለት ሳምንታት በፊት የጃፓንን የአየር ክልል ጥሶ ያለፈ የባላስቲክ ሜሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።

የመጀመሪያ የባላስቲክ ሚሳኤል ወደ ላይ 550 ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘ ሲሆን፥ 2 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ ነበር ባህር ውስጥ የወደቀው።

Advertisement