NEWS: በአዋሽ ተፋሰስ ከፍተኛ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለፀ

                               

በበላይ ተስፋዬ

እየጣለ ያለው ዝናብ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ ከፍተኛ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአዋሽ ተፋሰስ ባለሰልጣን አሳሰበ።

ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጸው፥ በተለይ የቆቃ ግድብ በመሙላቱ ከፍተኛ ውሃ ወደ ወንዙ እየተቀላቀለ ይገኛል።

ከሚለቀቀው ውሃ በተጨማሪ ከቆቃ ግድብ በታች ካሉ ገባር ወንዞች ጋር በመሆን በአካባቢው ጎርፍ እንዲከሰት የማድረግ አቅም እንዳለውም ጠቅሷል።

በመሆኑም በወንዙ አከባቢ ያሉ የምስራቅ ሸዋ ዞን የአዳማና ፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች እንዲሁም ከአርሲ ዞን መርቲና ጀጁ ወረዳ፣ ከአፋር ክልል ደግሞ በአሚባራ፣ ዱለቻ፣ ቡሬሙ ዳይቱና ገዋኔ ወረዳዎች የአዋሽ ወንዝን ተጠግተው የሚኖሩ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

ወንዙ ከሚኖረው ከፍተኛ ፍሰት የተነሳ በዳርቻው ያሉ ዛፎች ሊወድቁና የወንዙን አቅጣጫ ሊያስቀይሩ የሚችሉ በመሆኑ፥ በመስኖ የሚያለሙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲጠነቀቁ ነው ባለስልጣኑ ያሳሰበው።

የአካባቢው ነዋሪዎች የወንዝ አቅጣጫ ሊያስቀይሩ የሚችሉ ነገሮችን በማፅዳት አደጋውን ለመከላከል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።

በአዋሽ ተፋሰስ ከቆቃ ግድብ በላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ እንደሚኖር ታሳቢ አድርገው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው ብሏል።

ወንዙን በተለያዩ የልማት ስራዎች የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይከሰት፥ በንቃት ሊከታተሉ ይገባል ተብሏል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

 

 

 

Advertisement