NEWS: ወርቅ በሚመረትባቸው 5 ክልሎች የወርቅ የግብይት ማዕከላት ግንባታ ተጠናቀቀ

                          

በታሪክ አዱኛ

 በብዛት ወርቅ በሚመረትባቸው አምስት ክልሎች የመጀመርያ የወርቅ የግብይት ማዕከላት ግንባታ ተጠናቀቀ።

የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የግብይት ስርአቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ማዕከላቱ እንዲገነቡ አድርጓል።

በ2009 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ የወርቅ ምርት 231 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን በ2008 ዓ.ም ከተገኘው 309 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ያነሰ ነው።

ከወርቅ ግብይት ለሚገኘው ምንዛሪ ማነስ ደግሞ በማዕከላት ያለው ችግር ተጠቃሽ ነው ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ወርቁን ከማህበር ከተደራጁ ዜጎች ለመግዛት የተለያዩ ማእከላት በክልሎች ቢኖሩትም፥ በስራ ላይ ያሉት ማእከላት ከወርቅ አቅራቢዎች የሚርቁ በመሆኑ የሚታሰበውን ግብ አልመቱም።

አምራቾች ወርቁን ይዘው ሩቅ መንገድ መሄዳቸው የሚፈጥርባቸው ስጋት በራሱ ለኮንትሮባንድ ትልቅ ዕድልን ፈጥሯል። 

የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር ተወካይ አቶ ኪሮስ አለማየሁ፥ የግብይት ሰንሰለቱ ከመርዘም ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም ችግርና ዘርፉን የሚደግፍ መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ አለመኖሩ የግብይት እጥረት እንመዲያጋጥም ካስቻሉ ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው ብሏል።

የቤኒሻነጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ሃብት ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታነህ ሻዲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በርካታ ወርቅ በሚመረትበት ሸጎሊ ወረዳ የምርቱን መረከቢያ መገንባቱን ገልፀው ማእከሉ ከዚህ በፊት ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች እንደሚያጠቃልል ጠቁሟል።

በኦሮሚያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀነሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው፥ በክልሉ በሚገኙ የወርቅ አምራች አካባቢዎች የወርቅ ግብይቱ በአቅራቢያቸው መገንባቱ አምራቾቹ ተነሳሽነት በመፍጠር በቀላሉ አምርተው እንዲያሰረክቡ ያስችላል ብሏል።

እነዚህ በክልሉቹ የተገነቡ የወርቅ ማስረከቢያ ማዕከላት በ2010 በጀት ዓመት ወደ ግብይት ስርዓት ይገባሉ ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ሶስት የወርቅ አምራች ኩባንያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በ2010 አቅም ያላቸው ማህበራትን በመለየት ምርታቸውን ወደ ውጪ የሚልኩበት ስርዓት ይዘረጋል ነው ያለው።

ምንጭ :- FBC ኤፍ.ቢ.ሲ)

 

Advertisement