NEWS: ከጣና ሃይቅ የእምቦጭ አረምን የማስወገዱ ስራ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ቀጥሏል

                                    

በጣና ሃይቅና በአባይ ወንዝ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ሕብርተሰቡን ባሳተፈ መንገድ የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ የአካባቢ ደን፣ ዱር እንስሳትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ኃላፊ ዶክተር በላይነህ አየለ እንዳስትወቁት ከሀይቁ ውሃ መጨመር ጋር ተያይዞ አረሙ የሚወረው ቦታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።

በሀይቁ ዙሪያ በሚገኙ የደቡብና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ተከስቶ የነበረው አረም በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር ዙሪያ በሚገኘው የአባይ ወንዝ ላይ ጭምር በአዲስ መልክ መስፋፋቱ ተገልፀዋል።

ኃላፊው አረሙን ለመከላከል እስካሁን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መተግባር ባይቻልም የሕብረተሰቡን ጉልበት በመጠቀም የመንቀልና የማስወገድ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ሃይቁንና የአባይን ወንዝ የወረረውን 3 ሺህ ሄክታር የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።

አረሙ ፍሬውን አፍርቶ ከመበተኑ በፊት በዚህ ወር ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የተጀመረውን የዘመቻ ሥራ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው።

አረሙን ማስወገድ የጣናንና የአባይን ህልውና መጠበቅ በመሆኑ ሕብረተሰቡ የጀመረውን የማረም ሥራ አጠናከሮ መቀጠል አንዳለበት ኋላፊው አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ አየነው በላይ በበኩላቸው፣ “በአባይ ወንዝ 25 ሄክታር ክልል የተከሰተውን የእምቦጭ አረም የማስወገድ ሥራ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተጀምሯል” ብለዋል።

በአባይ ወንዝ በ25 ሄክታር ላይ አዲስ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በነገው ዕለት የባህር ዳርንና ዙሪያውን ሕብረተሰብ በማሳተፍ የማጽዳት ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል።

ዘመቻውን መሰረት በማድረግ በተያዘው ወር በባህር ዳር ዙሪያ በአባይ ወንዝ፣ በጣና ጭርቆስና በጎርጎራ አካባቢዎች ሕዝቡን በዘመቻው ለማሳተፍ ዝግጅት መደረጉም ነው የተጠቆመው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

 

Advertisement