ሰዎች በየትኛው የእድሜ ክልል ላይ ሙሉ ደስተኛ ይሆናሉ?

                                                

ሰዎች በየትኛው የእድሜ ክልል ላይ በህይወታቸው ሙሉ ደስተኛ ይሆናሉ የሚለውን ለማወቅ በርካታ ጥናቶች ይሰራሉ።

ከሰሞኑ በአንድ የአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት፥ ሰዎች ከ18 እስከ 25 ዓመት ባለው እድሜያቸው ሙሉ ደስተኛ እንደሚሆኑ ያሳያል።

ከዚህ የእድሜ ክልል ቀጥሎ ከ66 ዓመት በላይ ሲሆኑም በህይወታቸው ሙሉ እርካታ የሚያገኙበት መሆኑም በጥናቱ ተመላክቷል።

የዴኪን ዩኒቨርሲቲ የአውስትራሊያ የህይወት ስኬታማነት ማዕከል ባደረገው ቅኝት፥ ከ18 እስከ 25 ዓመት ውስጥ ሰዎች በጣም ደስተኛ የሚሆኑበት የእድሜ ክልል ሲሆን 66 ዓመት ሲሞላቸው ደግሞ በህይወታቸው ሙሉ እርካታ እንደሚያገኙ ይፋ አድርጓል።

አውስትራሊያውያኑ ከ66 ዓመታቸው በኋላ ጡረታ ቢወጡና የቤተሰብ ሃላፊነትና እርጅና ጫና ቢፈጥርባቸውም በህይወታቸው ላይ እሮሮና ማማረር ፈፅሞ አይታይም ይላል የጥናቱ ግኝት።

የዴኪን ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ዴሊሴ ሀቺንሰን እንደተናገሩት፥ ለሰዎች አጠቃላይ የኑሮ ስኬትና ደስተኛ መሆን የፋይናንስ አቅም፣ ጠንካራ ግንኙነት እና ያላቸው የህይወት መርህ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

ተመራማሪው በአውስትራሊያ በእርጅና የእድሜ ክልል በሚገኙ ሰዎች ላይ በተሰራው ዳሰሳ በራሳቸውና በልጆቻቸው ቀጣይ የገቢ ምጣኔ ዙሪያ እንደማይጨነቁና በህይወታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

የጥናቱ አመላካች ግኝት ከሶስት አውስትራሊያውያን መካከል ሁለቱ ኑሯቸው ሙሉ መሆኑን በደስታ ስሜት እንደሚናገሩ ያሳያል።

ከወላጆች መካከል 70 በመቶ ያህሉ ልጆቻቸው በቀጣይ ህይወታቸው ሙሉ ደስተኛ እንደሚሆኑና ለኑሮ የሚያስፈልግ የፋይናንስ አቅም እንዳላቸው በልበሙሉነት ተናግረዋል።

የዴኪን ዩኒቨርሲቲ የአውስትራሊያ የህይወት ስኬታማነት ማዕከል በ2 ሺህ ሰዎች ላይ ነው የዳሰሳ ጥናት ያደረገው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement