NEWS: ሚኒስቴሩ የህክምና መሳሪያዎች ጠጋኝ ባለሙያዎችን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እያሰለጠነ ነው

                              

የህክምና መሳሪያዎችን መጠገን የሚችሉ ባለሙያዎችን ለማፍራትና የጥገና ማዕከላት በየህክምና ተቋማቱ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልፀ።

በመንግስት የህክምና ተቋማት የመመርመሪያ መሳሪያዎች ችግር መኖሩ ታካሚዎች በግል ተቋማት ከፍተኛ ገንዘብን እንዲያወጡ እያስገደደ ነው።

ከዚህም ባሻገር ህመሙ በበቂ ሁኔታ እንዳይታከምና ወደ ባሰ ደረጃ እንዲያድግ የመሳሪያዎች ብልሽት አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል ታካሚዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሀገሪቱ ከፍተኛ በጀት እየመደበች የህክምና መሳሪያዎችን ብትገዛም መሳሪያዎቹ የአገልግሎት ዘመናቸውን ሳይጨርሱ፥ ሲበላሹ የሚጠግናቸው ባለሙያ ለማፍራት ትኩረት ባለመሰጠቱ ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚደርስ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በመሳሪያ ብልሽት ምክንያት ከሚስተጓጎለው አገልግሎት ባሻገር፥ በየህክምና ተቋማቱ ቅጥር ግቢዎች ወድቀውና በመጋዘኖች ታጭቀው የሚታዩት የህክምና መሳሪያዎችም የዚህ ውጤት ናቸው።

የመሳሪያ ጥገና ባለሙያ እጥረትና የጥገና ማዕከል አለመገኘት ደግሞ በአገልግሎት ጥራት ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንደሚፈጥር ነው ባለሞያዎች የገለጹት።

በአለርት ሆስፒታል የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሩ አብርሃም ዘነበ፥ የህክምና መሳሪያዎች ብልሽት ሲያጋጥማቸው ብቻ ሳይሆን ያሉበትን ደረጃ በመገምገም በትክክለኛው ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ በባለሙያ መረጋገጥ አለበት ይላሉ።

አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም በሚጠበቀው ልክ አለመኖሩ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረጋትና ለመልካም አስተዳደር እጦት መንስኤ እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያምናል።

በሚኒስቴሩ የሚኒስቴር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ሃላፊና አማካሪ ዶክተር ዳንኤል ገብረ ሚካኤል፥ ችግሩ ተቋማቸው የህክምናን ጥራት ለማምጣት በሚያደርገው ሂደት ላይ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ይሰጥ የነበረው የመሳሪያ ጥገና ባለሙያዎች ስልጠና በ13 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠት መጀመሩን ነው የገለፁት።

ከስልጠናው ጎን ለጎንም ሆስፒታሎች በየራሳቸው የጥገና ማዕከላትን እንዲገነቡ ለማድረግ የጥገና መሳሪያዎች ግዥ እየተፈጸመ መሆኑን ዶክተር ዳንኤል ጠቁመዋል።

ችግሩን የመቅረፉ ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የህክምና መሳሪያዎች አያያዝና አጠቃቀም መመሪያ መዘጋጀቱን የገለፁት አማካሪው፥ መመሪያው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ስራ ላይ ሲውል በየተቋማቱ የሚታዩ ችግሮች ይቀንሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

 

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement