NEWS: ለጤና ጎጂ ለሆነው አፍላ ቶክሲን ተጋላጭ የሆኑ አምስት አይነት ምርቶችን ላይ ጥናት እየተደረገ ነው

                                                   

ትዕግስት ዘሪሁን

ለጤና ጎጂ ለሆነው አፍላ ቶክሲን ተጋላጭ የሆኑ አምስት አይነት ምርቶችን ከገበያ ላይ ናሙና ወስዶ በውስጣቸው ያለውን የአፍላ ቶክሲን መጠን እያጠና መሆኑን የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ተናገረ፡፡

በምግብ ውስጥ የሚገኝ አፍላ ቶክሲን የጉበት ካንሰርን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ድርጅቱ ለሸገር እንደተናገረው ለአፍላ ቶክሲን ሊጋለጡ ይችላሉ ተብለው ከተጠረጠሩና ናሙናቸው ከገበያ ላይ ተወስዶ ከሚመረመሩ ምርቶች መካከል ወተት አንዱ ነው፡፡

ፓስቼራይዝድ የሆኑ በየሱቁና በየሱፐርማርኬቱ ከሚሸጠው ወተት በተጨማሪ ከግለሰብ ቤቶችም የላም ወተት ለናሙና ተወስዶ እየተመረመረ መሆኑን የድርጅቱ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተሻለ በልሁ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

በርበሬ፣ ሽሮ፣ የለውዝ ቅቤና የበሶ ዱቄትም ናሙናቸው ከገበያ ላይ ተወስዶ ለጤና ጎጂ የሆነው አፍላ ቶክሲን በውስጣቸው ስለመኖር አለመኖሩ እየተጠና ነው ተብሏል፡፡

ወተትን፣ ከብቶች የሚመገቡት የምግብ አይነት እንደ በርበሬና ሽሮ ያሉ ምርቶች ደግሞ የአቀማመጥ ችግር ለአፍላ ቶክሲን ያጋልጣቸዋል ብለዋል፡፡

በምርቶቹ ላይ የተጀመረው ጥናት ሲጠናቀቅም ውጤቱ ለሚመለከተው ተቋጣጣሪ መሥሪያ ቤት ይፋ እንደሚደረግ አቶ ተሻለ ነግረውናል፡፡

በጥቂት ናሙና የተጀመረው ጥናት ውጤቱ ከታወቀ በኋላ በመጪው ጊዜ ሰፋ ያለ ጥናት ይደረጋልም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተሻለ እንደነገሩን ድርጅቱ ምርቶቹን ከገበያ ላይ ወስዶ ለጤና ጎጂ የሆነውን አፍላ ቶክሲን ስለ መያዝ አለመያዛቸው ጥናት የሚያደርገው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ነው ብለዋል፡፡

ለጥናቱም ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ሰምተናል፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

 

Advertisement