NEWS: የኢትዮጵያ አየር መንገድ የናይጀሪያውን አሪክ አየር መንገድ የማስተዳደር ስራ ሊረከብ ነው

                                                    

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የናይጀሪያውን አሪክ አየር መንገድ የማስተዳደር ስራ ለመረከብ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ድርድር እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አሪክ አየር መንገድን ለማስተዳደር እየተደረገ ባለው ድርድር በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መግባባት መደረሱን ተናግረዋል፡፡

የናይጀሪያ አየር መንገድ በ2012 በደረሰበት ኪሳራ ከተዘጋ ወዲህ ሀገሪቱ ብሔራዊ አየር መንገድ የላትም፡፡

ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የናይጀሪያ መንግስት ከሌሎች ጋር በሽርክና የመሰረተው ቨርጂን ናይጀሪያ እና የናይጀሪያ አየር መንገዶች በደረሰባቸው ኪሳራ ምክንያት መዘጋታቸው ይታወሳል፡፡

የናይጀሪያ መንግስት በአሁኑ ወቅት በግል ሲተዳደር የነበረውን አሪክ አየር መንገድ ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ ወደ መንግስት ይዞታ በማዞር እያስተዳደረው ይገኛል፡፡

ይህን ተከትሎም አየር መንገዱን ትርፋማ ለማድረግ የናይጀሪያ መንግስት የማስተዳደር ስራውን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለማስረከብ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የናይጀሪያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጎድፍሬይ ኦዱዲግቦ፥ አየር መንገዱን በውል ለማሳተዳደር እየተካሄደ የሚገኘው የሁለቱ ወገኖች ድርድር በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቴክኒክ ድጋፎችን የሚሰጥበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ኦዱዲግቦ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የናይጀሪያና የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመመስረት የጋራ ኮሚሽን መመስረታቸውን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል፡፡

በጋራ ኮሚሽኑ በሚደረጉ ስብሰባዎችም የተለያዩ የሁለትዮሽ ስምምነቶች የሚካሄዱ ሲሆን፥ የአሪክ አየር መንገድን የማስተዳደር ስምምነትም ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የጠቆሙት፡፡

እንደ አምባሳደሩ አገላለፅ የጋራ ኮሚሽኑ ስብሰባ በመጪው ህዳር ወር በአቡጃ ሲካሄድ አየር መንገዱን የማስተዳደር ስምምነት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራው ኢንዱስትሪ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ኦዱዲግቦ፥ የአሪክ አየር መንገድን ማስተዳደሩ የሀገሪቱ የአየር መንገዶች ህልውና እንዲረጋገጥና የአገልግሎት አድማሳቸው እንዲሰፋ ያስችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement