ለጭንቀት የተጋለጡ ሴቶች ፅንሳቸው የመጨናገፍ እድሉ 42 በመቶ ይደርሳል::

                                                 

ለረጅም አመታት ለጭንቀት የተጋለጡ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ፅንሳቸው የመቋረጥ እድሉ 42 በመቶ እንደሚደርስ አንድ ጥናት አመለከተ።

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እና በቻይና በሚገኘው ዠጃንግ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የተደረገው ጥናት በወጣትነታቸው ጭንቀት የሚያበዙ ሴቶች በኋለኛው እደሜያቸው በርካታ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው አረጋግጧል።

በጥናቱ ጭንቀት እና ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥማቸው የፅንስ መጨናገፍ ያላቸው ግንኙነት ተዳሷል።

ሴቶች ከፀነሱ ከ24 ሳምንታት በፊት የሚከሰተው የፅንስ መጨናገፍ፥ በእያንዳንዱ ነፍሰ ጡር ሴት የመድረስ እድሉ 20 በመቶ ነው።

ሴቶች በእርግዝና ወቅት ስለ ትዳር አጋራቸው፣ ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሲገቡ የፅንስ መጨናገፍ እንደሚከሰት ነው ጥናቶች የሚያሳዩት።

የማህበራዊ ግንኙነት ችግር፣ የገቢ ማነስ፣ በትዳር አለመደሰት፣ በስራ ገበታ የሚያጋጥም ጫና እንዲሁም ከዚህ ቀደም ያጋጠመ የፅንስ መጨናገፍም ሌሎች አበይት ምክንያት ናቸው ተብሏል።

በለንደን ዩኒቨርሲቲ እና ዠጃንግ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት የጭንቀት እና ፅንስ መጨናገፍ ዝምድና የጭንቀት ሆርሞኖች ከመመንጨታቸው እና መለቀቃቸው ጋር ይያያዛል ይላል።

እነዚህ የጭንቀት ሆርሞኖች ለፅንሱ እድገት ወሳኝ የሆኑ ኬሚካሎች እንቅስቃሴን ያውካሉም ነው ያለው ጥናቱ።

የጥናቱ ዋና አዘጋጅ እና በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የስነ ልቦና አስተማሪ የሆኑት ዶክተር ብሬንዳ ቶድ፥ ከእርግዝና በፊት አልያም በኋላ የሚከሰት ከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ጭንቀት ከፅንስ መጨናገፍ ጋር ሰፊ ግንኙነት እንዳለው አረጋግጠናል ብለዋል።

ጥናቱ በተለይም በወጣትነት እድሜያቸው ለጭንቀት የተዳረጉ ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚገጥማቸው የፅንስ መጨናገፍ ችግር ወደ 42 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችልም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሴቶች ከማርገዛቸው በፊት ስነ ልቦናዊ የጤና ሁኔታቸውን ቢያውቁት መልካም ነው ብለዋል።

ጥናቱ የጭንቀት እና ፅንስ መጨናገፍ ዝምድናን ያመላከተ ቢሆንም በቀጣይም ሌሎች ጥናቶች ሉደረጉ እንደሚገባም ነው ዶክተር ቶድ ያብራሩት።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement