ዘረኞች በአደባባይ

                                  

ኤፍሬም እንዳለ

‘ዘ ተርነር ዳያሪስ’ የሚባል መጽሐፍ አለ፡፡ የነጭ የበላይነትን ማስፈን ስለሚፈልግ የሽምቅ ተዋጊ ቡድን የሚተርክ ልብ ወለዳዊ ሥራ ነው፡፡ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ‘የገመዱ ዕለት’ የሚል ምእራፍ አለ፡፡

አሜሪካ በፍጹማዊ የነጭ የበላይነት መንግሥት ሥር ስትሆን ምን እንደምትመስል የሚተርከው ክፍል ውስጥ እንዲህ የሚል አረፍተ ነገር ይገኛል… “ሰዎች ከቤታቸው ወደ ውጪ ወጥተው ሲመለከቱ ዓይናቸው እስከደረሰ ድረስ በመንገድ መብራት ምሰሶዎች ላይ ሰዎች በገመድ ተንጠልጥለው ያያሉ፡፡”

የነጭ የበላይነት አራማጆች ስልጣን ቢይዙ አሜሪካ ምን እንደምትመስል የሳሉት ምናባዊ ስዕል፡፡

በነገራችን ላይ፣ ‘ዘ ተርነር ዳያሪስ’ የነጭ ዘረኞች መጽሐፍ ቅዱስ ነው ይሉታል፡፡ በ2042 በአሜሪካ ከነጮች ይልቅ ነጭ ያልሆኑት ሰዎች በቁጥር ይበልጣሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡ “እንዲህም ስለሆነ፣” ይላሉ የነጭ የበላይነት አራማጆች፣ “ነጮች የራሳቸው የሆነ አገር ያስፈልጋቸዋል፡፡”

በእርግጥም አስፈሪ ነው፡፡ አንዳንድ የነጭ የበላይነት አራማጆች ዘር ማጥፋትና የዘር ማንጻትን ይሰብካሉ ተብሏል፡፡ እንዲህ አይነት ቡድኖችን የምትከተታል ሴት ስለ ነጭ ዘረኞች መንግሥት እንዲህ ብላለች… “አምባገነን መንግሥት ይሆናል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ስልጣን በነጮች እጅ ይሆናል፡፡ ስለ አሜሪካ መጻኢ እድል ያላቸው ራዕይ የአስራ ስድተኛውና ከዛም በፊት የነበረ ክፍለ ዘመንን ይመስላል፣” ብላለች፡፡ እነዚህ ዘረኞች ዋና መለያቸው ጥቁሮችንና ይሁዲዎችን ይጠላሉ፡፡

ሂትለርን ያደንቃሉ፣ የናዚም ሰላምታ ይሰጣሉ፡፡ የሚያውለበልቧቸው ባንዲራዎች አፍቃሪ ባርነት የነበረውና በአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት የተሸነፈው ኮንፌዴሬሲ ባንዲራዎች ናቸው፡፡

እንግዲህ ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካዋ ቨርጂንያ ግዛት በቻርሎትስቪል ከተማ ግልጽ የዘረኝነት መልእክታቸውን ይዘው አደባባይ የወጡት ግለሰቦችና ቡድኖች ቀደም ብላ የተጠቀሰችውን ምናባዊ አሜሪካ ለመፍጠር የሚያልሙ ናቸው ተብሏል፡፡

ለበርካታ ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ትልቁ የጥላቻ ስብስብ ነው የተባለው፡፡ በሰልፉ ወቅት አንድ ነጭ አክራሪ በመኪናው ተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ወጥቶ አንዲት ሴት ስትሞት 19 ያህል ቆሰሉ፡፡ በብጥብጡም ሌሎች 15 ያህል ሰዎች ቆስለዋል፡፡

በሄሊኮፕተር ቅኝት እያደረጉ የነበሩ ሁለት ፖለሲችም ሄሊኮፕተራቸው ተከስክሳ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ይህ የዘረኞቹ ሰልፍና የተከተለውም ሁከት ከተለያዩ ወገኖች ተወግዟል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የዘረኞቹ ድርጊት አይበቃ ይመስል ነገሩን ያጦዘው የ45ኛው የአሜሪካ ፐሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ አስተያየት ነበር፡፡

“በብዙ ወገኖች የታየውን ይህን አስደንጋጭ ጥላቻ፣ ጠባብነትና ጠበኝነት አጥብቀን እናወገዛለን” ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ፡፡ አገር ያመሰውም ይህ አባባል ነው፡፡

“በብዙ ወገኖች” ማለት ምን ማለት ነው? ብጥብጡን የጀመሩት፣ በመፈክርና በዘረኛ ስድቦች ግልጽ ጥላቻና ጠባብነቱን ያንጸባርቁ የነበሩት ነጮቹ ዘረኞች ሆነው ሳለ ትረምፕ እነሱን ፊት ለፊት በስም ጠቅሰው ያላወገዙት ለምንድነው ? አካፋን አካፋ ለማለት ድፍረቱ ያልነበራቸው ለምንድነው? የበርካታ አሜሪካውያን ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ምክትላቸው ማይክ ፔንስና ልጃቸው ኢቫንካ ዘረኛ ቡድኖቹን በስም ጠቅሰው አውገዘዋል፡፡ የትረምፕ ደጋፊ የሚባሉት ሴናተር ኮሪ ጋርድነርም፣ “ሚስተር ፕሬዝደንት፣ ክፉ ነገርን በስሙ መጥራት አለብን፡፡ እነኚህ የነጭ የበላይነት አራማጆች ነበሩ፣ ድርጊቱም የአገር ውስጥ ሽብርተኝነት ነበር፣” ብለዋል፡፡

ሴናተር ኦሪን ሀች የተባሉት ደግሞ “የእኔ ወንድም ሂትለርን ሲፋለም ህይወቱን የሰዋው የናዚ ሀሳቦች እዚህ አገራችን ያለተቃውሞ እንዲስፋፉ አይደለም፣” ብለዋል፡፡ ከኋይት ሀውስም ‘ፕሬዝዳንቱ የነጭ የበላይነት አራማጆችን፣ ኬ.ኬ.ኬ.ን፣ አፍቃሪ ናዚዎችን እና አክራሪ ቡድኖችን ያወግዛሉ’ የሚል መግለጫ ወጣ፡፡

“እንዲህ ከሆነ ታዲያ ፕሬዝደንቱ ራሳቸው ይህን ለመናገር አንደበታቸውን ምን ለጎማቸው?” መልስ የሰጠ የለም፡፡ እንደውም መግለጫውን ያሰራጨችው የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ማንነቷን እንኳን ለመግለጽ አልፈለገችም፡፡

የ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ እንቅስቃሴ፣ መሣሪያ ያልታጠቁ አፍሪካ አሜሪካውያን በየመንገዱ በፖሊስ መገደላቸውንና በአጠቃላይ አፍሪካ አሜሪካውያን ላይ እየተባባሰ የመጣውን ዘረኝነት በመቃወም በጥቁሮቹ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ትረምፕ ተሳታፊዎቹን ምን ቢሏቸው ጥሩ ነው… “ዘረኞች!” – ከፖሊስ ጋር ለተፈጠረ ግጭትም ጥፋተኛ ያደረጉት ተበዳዮቹን ነው፡፡

እንደውም በቅርቡ ለፖሊሶች ባደረጉት ንግግር “ይሄን ያህልም ደግ አትሁኑ፣” ማለታቸው ፖሊስ ለሚወስደው ከልክ ያለፈ እርምጃ በተዘዋዋሪ ይሁንታ መስጠታቸው ነው ተብሏል፡፡

እንግዲሀ ዘረኝነትን በመቃወም የወጡትን ጥቁሮች “ዘረኞች፣” ያሏቸው ሰው ናቸው፤ የዘረኝነትን የጥላቻን መልእክት ይዘው የወጡትንና ዘረኝነታቸውን በግልጽ የሰበኩትን ነውጠኞች በስም ጠርተው ለማውገዝ ያልሞከሩት፡፡

ፕሬዝደንቱን “የሥራህን ይስጥህ!” ብለው ያማረሯቸውን ያህል “ኢሮ!” ብለው ያጨበጨቡላቸው አሉ፡፡ ‘ዴይሊ ስቶርመር’ የተባለው የነጮቹ ዘረኞች ድረ ገጽ ትረምፕን “አንጀታችንን አራሰው” ብሏቸዋል፡፡ “እንዲያወግዝ ሲጠየቅ ዝም ብሎ ከክፍሉ ወጣ፡፡ በጣም፣ በጣም ጥሩ፡፡ እግዚብሔር ይባርከው..” ነበር ያለው ድረገፁ !

ረጅም ጊዜ የቆየውና ለበርካታ አስርት ዓመታት ለብዙ ጥቁሮች ሞት ዋና ምክንያት የሆነው ኩ ክሉክስ ክላን ወይም ኬ.ኬ.ኬ. የተባለው ዘረኛ ድርጅት መሪ የነበረውና የዘረኞች ቁንጮ ዴቪድ ዲዩክ ትረምፕን እንዲሀ ብሏቸዋል… “መስታወት ውስጥ ራስህን ተመልክተህ አንተን ፕሬዝደንት ያደረጉት ነጭ አሜሪካውያን እንጂ አክራሪ ግራ ክንፎች አለመሆናችውን አስታውስ፣” ብሏቸዋል፡፡

“ይህ ለእኛ አገር ሰዎች ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ አገራችንን መልሰን እጃችን ለማስገባት ቆርጠን ተነስተናል፡፡ ዶናልድ ትረምፕ ቃል የገባቸውን እናሳካለን፣ ያመንነበትም ይኸው ነው፡፡ ለዶናልድ ትረምፕ ድምጽ የሰጠነው ለዚህ ነው፣ አገራችንን በእጃችን መልሰን እናስገባለን ስላለ፣ ማድረግ ያለብንም ይኸንኑ ነው፡፡”

ትረምፕ “እዛው በጠበልህ፣ የምን ማነካካት ነው!” አላሉም፡፡ እንደውም የምርጫ ዘመቻቸው ጊዜ ዲዩክ በአደባባይ ለትረምፕ ድጋፉን ሲሰጥ ሰውየው “የአንተን ድጋፍ አልፈልግም” አላሉትም፣ ቆየተው ራሳቸውን ከእሱ ለማራቅ ሞከሩ እንጂ፡፡ በተጨማሪም ዘረኞችና ጥላቻን የሚያባባሱ ቡድኖች እሳቸውን በሚደግፉበት ወቅት አፍ አውጥተው አልተቃወሙም፡፡

ብሬይባርት እና ኢንፎዋርስ የተባሉ የቀኝ ክንፍ የሚዲያ ተቋማት ድጋፍም ነበራቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት በምርጫ ውድድሩ ወቅት ትረምፕን ከመደገፋቸው በላይ ተቃዋሚዎቻቸውን ደግሞ ወገንተኛ በሆኑ የሀሰት መረጃዎች ሲያጣጥሏቸው ነበር፡፡

ነጭ ዘረኞች በቅርብ ጊዜያት በድፍን አሜሪካ ጥቃቶች እንዲባባሱ አድርገዋል ተብሏል፡፡ እንደ ምሳሌ የተጠቀሱትም ግንቦት ላይ ፖርትላንድ፣ ኦሬጎን ውስጥ አንዲት የ16 ዓመት ወጣትንና ሙስሊም ጓደኛዋን ከዘረኞች ጥቃት ለመከላከል የሞከሩ ሁለት ሰዎች በጩቤ ተወግተው የተገደሉበት፣ በዛው ወር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ ውስጥ አንድ ጥቁር ተማሪ በጩቤ ተወግቶ የሞተበት፣ መጋቢት ውስጥ ኒውዮርክ ውስጥ የ60 ዓመት ጥቁር አሜሪካዊ እንዲሁ ተወግተው የተገደሉበት ይጠቀሳሉ፡፡

በነገራችን ላይ ከዘረኛ ነጮች ቡድኖች መሀል ‘ስኪንሄድስ’ የሚባሉትን በተመለከተ ከእኛ ዜጋ ጋር የተያያዘ ታሪክ አለ፡፡ በ1998 በአንዲት እርጥበታማ የህዳር ምሽት ፖርትላንድ ውስጥ የሆነ ነው፡፡ ሙሉጌታ ስራው የተባለ የ27 ዓመት ወጣት ጓደኞቹ ቤቱ በራፍ ላይ ከመኪና አውርደውት እየተሰነባበቱ ነበር፡፡ መኪና ሙሉ ኒኦናዚዎች ይደርሱባቸዋል፡፡

ከመኪናው ውጪ የነበረው ሙሉጌታ ላይ የስድብ ናዳ ያወርዱበታል፡፡

በዚህ መሀል አንዱ በቤዝቦል ዱላ አናቱን ይለዋል፡፡ ወጣቱም ህይወቱ ያልፋል፡፡ በወቅቱ ይህ የዘረኝነት ጭካኔ የድፍን አሜሪካ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

የቅዳሜው ሰልፈኞች መልእክት ግልጽ ነው – ነጭ ያልሆኑትን በተለይ ደግሞ ጥቁሮችን ማጥፋት፣ ምናለባትም ‘ዘ ተርነር ዳያሪስ’ መጽሀፍ ላይ እንደሰፈረው የእኛ አይደሉም የሚሏቸውን በየመንገዱ መብራት ምሰሶ ላይ ማንጠልጠል፡፡

የሰልፉ አንዱ አስደንጋጭ ነገር ዘረኞቹ ማነንታቸውን ለመደበቅ አለመሞከራቸው ነው፡፡ ለወትሮው እንደ ኬ.ኬ.ኬና ሌሎች መሰል ቡድኖች አባላት ፊቶቻቸውን በጭምብል ይሸፍኑ ነበር፡፡ አሁን ግን እንዲህ በግልጽ አደባባይ መውጣታቸው ምንም እንደማይደርስባቸው ስላወቁና በዶናልድ ትረምፕ የልብ ልብ ስላገኙ ነው ተብሏል፡፡

እንደውም የናዚዎችን ‘ብለድ ኤንድ ሶይል’ (ደምና አፈር እንደማለት) የሚል መፈክር ያሰሙ ነበር፡፡ አሁን በአሜሪካ የሰፈነውን የፖለቲካ ምስቅልቅል ለራሳቸው ጥቅም መጠቀም ይፈልጋሉ ይባላል፡፡ 
በተጨማሪም የጦር ሜዳ የብረት ቆብ ከማድረግ ጀምሮ ጠብመንጃና የተለያዩ መሣሪያዎች መታጠቃቸው ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር፡፡

ሳውዘርን ፖቨርቲ ሎው ሴንተር የተባለ ታዋቂ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ከ1‚600 በላይ የሆኑ ጽንፈኛ ቡድኖችን እንቅስቃሴ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል፡፡

እንግዲህ ነገሩ ፕሬዝደንቱ ምን አሉ፣ ምን አላሉ ከሚለው እያለፈ ነው፡፡ አሜሪካ አደጋ ላይ ነች፡፡ የጸረ ስደተኞች ዘረኝነቱ እየተባባሰ ነው፡፡ የአሜሪካ ፖሊሲ ይበልጡኑ ሌላውን ያገለለ እየሆነ ነው፡፡

የድንበር ግምብ መገንባቱ፣ የጉዞ እገዳው፣ ሰዎችን በብዛት ወደ አገራቸው ማባረሩ የመሳሰሉት እርምጃዎች ከአስርና ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት በነጭ የባለይነት አራማጆች ድረገጾች ላይ ይለጠፉ የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡

አሁን በትረምፕ ዘመን እነኚህ ነገሮች ፖሊሲ ሆነዋል፣ እየሆኑም ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዘረኝነት በማባባሱ ውስጥ ማህበራዊው ሚዲያ ቀላል የማይባል ሚና እየተጫወተ ነው ተብሏል፡፡

ሳውዘርን ፖቨርቲ ሎው ሴንተር የተባለ የታወቀ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ከ1‚600 በላይ የሆኑ ጽንፈኛ ቡድኖችን እንቅስቃሴ እየተከታተለ ነው መባሉ፤ ነገሩ የጥቂት ነውጠኞች ድርጊት ብቻ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

በመጨረሻ እንደሚባለው፣ በመጨረሻም፣ ማለትም ከድርጊቱ ሁለት ቀናት በኋላ ትረምፕ ዘረኛ ቡድኖቹን በስም ጠቅሰው አወገዙ፡፡ “ዘረኝነት የክፉዎች ድርጊት ነው፡፡ በእሱ ስምም ሁከት የሚፈጥሩት ወንጀለኞችና አመጸኞች ናቸው፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ በተደረገው የዘረኞች ሁከት ወንጀል የፈጸመ ሁሉ በህግ ይጠየቃል፣” አሉ፡፡

ትረምፕ ለዚህ ንግግራቸው ዳር እስከዳር ጭብጨባ ጠብቀው ከሆነ አላገኙትም፡፡ እንደውም ጋዜጠኞች ይህንን ለመናገር ለምን ይሄን ያሀል ጊዜ ወሰደብዎ?” አሉ፡፡ ትረምፕ መልስ አልሰጡም፡፡ በነገራችን ላይ አንዳንድ ክፍሎች ሰልፉ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን ማንነት በኢንተርኔት እየለቀቁ ነው፡፡

ውግዘቱ ቀጥሏል፡፡ ፕሬዝደንቱ ይህቺን ታክልም የተናገሩት ከሁሉም አቅጣጫ ጫናው ሰለበዛባቸው ነው ተብሏል፡፡ ደግሞም ነገሩ ‘ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ’ ነው፡፡ በግልጽ “የነጭ ብሄረተኞችን፣ የዘረኞችንና የጠባቦችን ድጋፍ አልፈልግም” አለማለታቸው “ሰውየው ከልቡ አይደለም፣” እያስባላቸው ነው፡፡

ዴቪድ ዲዩክም ዞሮባቸዋል፡፡ “ፕሬዝደንት ትረምፕ፣ እባክህ ስለ እግዚአብሔር ብለህ፡፡ እነኚህን ነገሮች መናገር ያለብህ አይመስለኝም – ምንም አይፈይድልህም፣” ብሏቸዋል፡፡

ምናልባትም ይህቺን የዴቪድ ዲዮክን ምክርም ሰምተው አልያል ከአቋሜማ አልፍረከረክምም ብለው ይሆናል – ማክሰኞ ዕለት ደግሞ የነጭ ዘረኞቹንና እነሱን ተቃውመው የወጡትን ፀረ-ዘረኞቹን እኩል ጥፋተኞች ናቸው ብለው አረፉት…

ለብዙዎች ሁኔታው አሳማሚ ነበር፡፡ ሴናተር ሊንደስሌይ ግርሃም፣ “የታላቁን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት፣ የሊንከን ፓርቲ ለዘረኞች አንጥፎ ሲቀበል ማየት አልፈልግም” ብሏል፡፡

ዘረኞቹ እንዲህ ግልጽልጽ ባለ መንገድ አደባባይ እንዲወጡ የልብ ልብ የሰጣቸው ዶናልድ ትረምፕ በየጊዜው የሚሰነዝሯቸው ዘረኛ አስተያየቶች ናቸው ተብሏል፡፡ “በእሱ ፕሬዝደንትነት እየተጠናከሩ የመጡት ነፍሰ ገዳይ ዘረኞች መሪ ነው፣” ብላለች አንዷ ተቺ፡፡ “በነፍስ ማጥፋት ሊከሰስ ይገባል” – አከለች !!!

ሆኖም የተቃውሞ ድምጾች ምንም ያህል ጎልተው ቢሰሙም የቅዳሜው ሰልፍ ያሳየው አንድ ነገር አለ፣ የዘረኞችን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ መጪዎቹ ጊዜያት ለአሜሪካ መልካም እንደማይሆኑ፡፡

በነገራችን ላይ እነኚሁ ዘረኛ ቡድኖች የመስከረሙ የአሜሪካ የሽብር ጥቃት በሚታሰብበት እለት ታላቅ ሰልፍ ለማድረግ እያቀዱ ነው ተብሏል፡፡ እውነት እንዳሉት የሚሰለፉ ከሆነም የጸረ—ዘረኝነት ቡድኖችም ሀይላቸውን አጠናከረው መውጣታቸው አይቀርም ነው የሚባለው፡፡

አሜሪካም ትንፋሿን ውጣ እየጠበቀች ነው…

Advertisement