NEWS: በዓለም ለመኖር የማይመቹ 10 ከተሞች ዝርዝር ይፋ ሆነ

                                    

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን የሚገኙ በርካታ ከተሞች በሽብርተኝነትና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት ለመኖር አስጊ እየሆኑ ነው።

በተለይም አይኤስ እና ቦኮሃራም በየአፅናፉ በተዘረጉባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ሰላም ዘወትር ስጋት ላይ ነው።

ኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት የተባለ የጥናት ቡድን በዓለም ለመኖር ምቹ የሆኑና አስጊ የሆኑ 140 ከተሞችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

የጥናቱ አመላካች ግኝት መሰረት ያደረገው ከተሞች ለሰላማዊ ኑሮ ምን ያህል ምቹ ናቸው የሚለውን በማመዛዘን ነው።

ለአብነትም የከተሞቹ የመረጋጋት ደረጃ፣ የጤና አገልግሎት፣ የባህልና አካባቢ አጠባበቅ፣ የትምህርትና መሰረተ ልማት ጉዳዮችን ጨምሮ 100 መስፈርቶች ግምት ውስጥ ገብተዋል።

በአውትራሊያ ኒው ዚላንድ እና በአውሮፓ የሚገኙ ከተሞች አሁንም ለኑሮ ምቹ በመሆን ቀዳሚውን ተርታ ይዘዋል።

በአንጻሩ የመካከለኛው ምስራቅ፣ የአፍሪካና እስያ ከተሞች እንዲሁም የአውሮፓዋ ኬቭ ለኑሮ አስጊ ተብብለዋል።

በዚህም መሰረት በ2017 ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ 10 ከተሞችን ዝርዝር በኑሮ አስጊነት ደረጃቸው ቅደም ተከተል መሰረት እንደሚከተለው ይፋ ሆነዋል፡፡

1. ደማስቆ-ሶሪያ

ደማስቆ አምና ካገኘችው 16 ነጥብ 2 ውጤት ብታሻሽልም፥ የጥናት ቡድኑ ካስቀመጣቸው 100 መስፈርቶች ውስጥ 30 ነጥብ 2 ብቻ በማሟላት

ዘንድሮም በዓለም ከተጠኑ 140 ከተሞች መካከል ለኑሮ ምቹ ባለመሆን ቀዳሚዋ ሆናለች።

2. ሌጎስ-ናይጀሪያ

በቦኮሃራም የሽብር ተግባራት ውሎና አዳሯ ስቃይ የሆነባት የናይጀሪያዋ ዋና ከተማ ሌጎስ፥ በዓለም ከተጠኑ ከተሞች ባለመረጋጋት ደረጃ ቀዳሚዋ ሆናለች።

ሆኖም በሌሎች አገልግሎቶች ከደማስቆ የተሻለ 36 ከመቶ በማግኘቷ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

3. ትሪፖሊ-ሊቢያ

የሊቢያዋ ከተማ ትሪፖሊ በሰሜንና ምስራቅ አፍሪካ በተሰገሰጉ አሸባሪ ቡድኖች ምክንያት የሰላም አየር መተንፈስ አልቻለችም።

በዚህና በሌሎች ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን ባለማሟላት፥ ከ100 መስፈርት 36 ነጥብ 6 ብቻ አሟልታ ለኑሮ ምቹ ባለመሆን በዓለም ካሉ ከተሞች በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

4. ደሃካ-ባንገላዲሽ

የባንግላዲሿ ዋና ከተማ ደሃካ በመሰረተ ልማት አገልግሎት መሟላት ከተሰጣት መስፈርት ውስጥ 26 ነጥብ 8 ከመቶ ያገኘች ሲሆን፥ ባለመረጋጋት ደግሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከተመደቡት ጎራ ተሰልፋለች።

በዚህም መሰረት ከተማዋ በአጠቃላይ ለኑሮ ምቹ ባለመሆንና በአስጊነት ደረጃ ተመድባ አራተኛ ደረጃን ይዛለች።

5. ፖርት ሞሬስቢ-ፓፓ ኒው ጊኒ

ይህች ከተማ በትምህርት፣ በባህልና በአካባቢ ጥበቃ ጥሩ ደረጃ ብታገኝም፥ የመረጋጋት ሁኔታዋ ግን 30 በመቶ ሆኗል።

በአጠቃላይም ከ140 ከተሞች ውስጥ ለኑሮ ምቹ ባለመሆን 39 ነጥብ 6 ከመቶ በማግኘት አምስተኛ ደረጃ ላይ ተመድባለች።

6. አልጀርስ-አልጀሪያ

የሰሜን አፍሪካዊቷ አልጀርስ ለነዋሪዎቿ ምቹ የትምህርት አገልግሎት በማቅረብ ብትመሰገንም፥ በመሰረተ ልማቶቿ ግን ትችት ወስጥ ገብታለች።

ከተማዋ በአጠቃላይ ያገኘችው ውጤት 40 ነጥብ 9 በመሆኑ በዓለም ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ ከተማ በሚለው ዝርዝር ውስጥ ስድስተኛ ላይ ተገኝታለች።

7. ካራቺ-ፓኪስታን

ካራቺ በማህበራዊና ፖለቲካዊ መረጋጋት ያስመዘገበችው ውጤት እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን፥ በአንጻሩ በትምህርት አቅርቦት ደግሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በአጠቃላይ ለነዋሪዎቿ ምቹ በመሆን ደረጃ ያገኘችው ነጥብ 40 ነጥብ 9 በመቶ በመሆኑ፥ በዓለም ከተዘረዘሩት ከተሞች ውስጥ ለኑሮ አስጊ ከተባሉት ምድብ በሰባተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

8. ሃራሬ-ዚምባብዌ

የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤዋ ሀገር ዋና ከተማ ሃራሬ በዓለም ለኑሮ አስጊ ከሆኑት ከተሞች ውስጥ 42 ነጥብ 6 ከመቶ መስፈርቶችን በማሟላት ስምንተኛ ሆናለች።

9. ዶዋላ- ካሜሩን

ካሜሩን በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች አካባቢ የተከሰተውን ውጥረት ተከትሎ፥ ዶዋላ ለነዋሪዎቿ አለመረጋጋትና ምቹ አለመሆን ምክንያት ሆናለች።

በዚህም መሰረት ከተቀመጡት 100 ነጥቦች ውስጥ 44 ብቻ በማሟላት ለኑሮ የማይመቹ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ዘጠነኛ ደረጃን ይዛለች።

10. ኬቭ-ዩክሬን

ኬቭ በ140 ከተሞች በተደረገው ቅኝት ከአውሮፓ ከተሞች መካከል ከተቀመጡት 100 መስፈርቶች ውስጥ ከ50 በታች ያገኘች ሆናለች።

ከተማዋ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና በማህበራዊ አለመረጋጋቶች ምክንያት 47 ነጥብ 8 ከ100 በማግኘት 10ኛዋ ለኑሮ ያልተመቸች ከተማ ሆናለች።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement