NEWS: በአዲስ አበባ ማስፋፊያ ያደረጉ ሆስፒታሎች የህክምና መሳሪያ አቅርቦት ችግር አሁንም አለመቀረፉን ያነሳሉ::

                                               

በትእግስት አብርሃም

በአዲስ አበባ ማስፋፊያ ያደረጉ ሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጣቸው ቢሻሻልም የህክምና መሳሪያ አቅርቦት ችግር በማስፋፊያቸው ልክ አገልግሎት እንዳይሰጡ እንቅፋት መሆኑን ያነሳሉ።

በአዲስ አበባ የሚገኙት የካቲት 12፣ ሚኒሊክ እና ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታሎች ማስፋፊያ አድርገዋል። 

ማስፋፊያውያ የሆስፒታሎቹ የአገልግሎት አይነት እና የሚያስተናግዷቸው ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ቢያደርግም፥ በማስፋፊያቸው ልክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል በቂ የህክምና መሳሪያ አቅርቦት አላስገኘላቸውም።

የየካቲት 12 ሚሊኒየም ኮሌጅ ሆስፒታል ፕሮቮስት ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል አበበ እንዳሉት፥ ማስፋፊያው የሆስፒታሉን ተመላላሽ ታካሚዎች ቁጥር ከ50 እስከ 60 ሺህ፣ አመታዊ የታካሚዎች ቁጥርን ደግሞ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ አድርሶታል።

188 የነበረው የአልጋ መጠንም ከ350 በላይ ሲሆን፥ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ይጠባበቁ የነበሩ ሰዎች ቁጥርም ዜሮ መሆኑን ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ የህክምና መሳሪያ አቅርቦት እጥረትና እና የተንዛዛ ግዥ ስርዓት አሁንም የሆስፒታሉ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል፤ ችግሩ ከመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ጋር የተያያዘ መሆኑን በመጥቀስ።

ይህን ተከትሎም ሆስፒታሉ የሚፈልገውን መሳሪያና የመድሃኒት አይነት በከፍተኛ ዋጋ ከግል በጨረታ እየገዛ መሆኑንም ተናግረዋል፤ ሁኔታው መንግስትን ኪሳራ ውስጥ እንደሚከት በማስረዳት።

የሚኒሊክ ሆስፒታልም ተመሳሳይ ችግር ነው የሚያነሳው ፤ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሽመልስ አለሙ እንደሚሉት ማስፋፊያው ሆስፒታሉ እንደ ህጻናት ህክምና እና የማዋለድ አገልግሎቶችን እንዲጀምር አስችሎታል።

ነገር ግን ሆስፒታሉ ያለበት የህክምና መሳሪያ አቅርቦት ችግር አዳዲስ አገልግሎቶችን በታቀደው ደረጃ እንዳይሰጥ አድርጎታል ነው የሚሉት፤ ከማስፋፊያው በኋላም ቢሆን ህሙማንን የሚያስተናግድበት የአልጋ ብዛት አሁንም አነስተኛ መሆኑን ያነሳሉ። 

ኤጀንሲው የህክምና መሳሪያ አቅርቦት ፍላጎቱን አለማቅረቡ ሳያንስም ከግል አቅራቢዎች መግዛት የሚያስችለውን ማረጋገጫ ለመስጠት ያለው የአሰራር ክፍተትም ሌላው ፈተና መሆኑን ዶክተር ሽመልስ ያስረዳሉ።

የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በበኩሉ፥ ከተቋማቱ የሚቀርበው የትላልቅ መሳሪያዎች አቅርቦት ጥያቄ ቀድሞ ለኤጀንሲው መቅረብ እና የ30 በመቶ የቅድሚያ ክፍያ መፈጸም አለበት ብሏል።

በዚህ ሂደትም ኤጀንሲው የግዥ ስርዓቱን ለመፈጸም ከስድስት እስከ ስምንት ወር እንደሚወስድበት የኤጀንሲው የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሞገስ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት፣ የታዘዙት ድርጅቶች እቃዎችን ቶሎ ካለማቅረብ እና ከሌሎች ተያያዥ ችግሮች ጋር በተያያዘ የኤጀንሲውን አገልግሎት አሰጣጥ እንዳጓተተበትም አስረድተዋል።

እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ ከፍተኛ ወጪ የማይጠይቁ የህክምና መሳሪያዎችን ተቋማት በጠየቁ ጊዜ ማቅረብ እንዲቻልም አዲስ አሰራር ተዘርግቷል፤ አሁን ላይም ከ250 በላይ የህክምና መሳሪያ አይነቶች ግዥ ለመፈጸም 94 ሚሊየን ዶላር ተመድቦ ጨረታ ወጥቷል ብለዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement