NEWS: በክረምት ዝግ ሆነው የሚቆዩት ፍርድ ቤቶች አስቸኳይ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት አገልግሎት ይሰጣሉ ተባለ፡፡

                                         

(ምህረት ሥዩም)

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደተናገረው ፍርድ ቤቶች የዜጎችን መብት የሚጥሱ አስቸኳይ ጉዳዮች ከገጠሙ በክረምቱ በመደበኛ እንዲሁም ተረኛ ችሎቶች የዳኝነት አገልግሎት ይሰጣሉ ብሏል፡፡

በክረምቱ ጊዜ በከፍተኛ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ ዳኞች የረፍት ጊዜያቸው በመሆኑ የዳኝነት አገልግሎት አይኖርም ተብሏል፡፡

ነገር ግን የዜጎችን መብት የሚጥሱና በሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ላይ ለሚገጥሙ አስቸኳይ የፍርድ ጉዳዮች ፍርድ ቤቶቹ በመደበኛ እንዲሁም ተረኛ ችሎቶች ጉዳዮችን ይመለከታሉ ተብሏል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክረምቱ ጊዜ የሙስና፣ ሽብር፣ ግድያ፣ ታክስ፣ አደንዛዥ ዕፅ፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን እንደሚመለከት ተናግሯል፡፡

የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች፣ የመያዣና የብርበራ ትዕዛዞች በክረምቱ መደበኛ የዳኝነት ችሎት የሚታዩ ጉዳዮች ሲሆኑ የጊዜ ቀጠሮ፣ የእምነት ቃል መቀበል ትዕዛዝ፣ የፍትሐ-ብሔር ጉዳዮች ከዋስትና ጋር የተያያዙ አቤቱታዎችና የእግድ ጉዳዮች በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተረኛ ችሎት ይስተናገዳሉ ተብሏል፡፡

የህፃናትን ጥቅማ ጥቅምና ደህንነት የሚመለከቱ ጉዳዮችም በሀገሪቱ በሚገኙ በ11 የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ምድብ ችሎቶች በክረምቱ ሳይቋረጡ የሚስተናገዱ የዳኝነት ጉዳዮች እንደሆኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሰበር የሚቀርቡ አቤቱታዎች እስከ ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም የሚስተናገዱ ናቸው ፤ ከዚህ ውጭ ያሉ ባለጉዳዮች ግን እስከ መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም የማትስተናገዱ መሆኑን እወቁት ተብላችኋል፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

 

Advertisement