NEWS: በከተማዋ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች በባለድርሻዎች አለመናበብ ምክንያት እየፈረሱ ነው ተባለ፡፡

                                                 

ምስክር አወል

የከተማዋ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአቅሜ በላይ የሆነ ነገር እየገጠመኝ ነውም ብሏል፡፡

ቤቶቹ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኘው የራስ አበበ አረጋይ ቤትና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ የሚገኘው የተፈጥሮ ሃብት ሙዚየም ናቸው፡፡

በቦታው ተገኝቶ አፍራሾቹን ለማስቆም የሞከረው የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አፍራሾቹ ኮንትራክተሮቹ አፍርሱ ተብለን ታዘን ነው የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ከቢሮው የህግ ጉዳዬች ባለሙያ አቶ አበበ ሳህሉ ሰምተናል፡፡

በአዲስ አበባ ቅርስነታቸው ታውቆ ይገባቸዋል ተብለው የተመዘገቡ 440 ቤቶች አሉ ያሉት አቶ አበበ ቅርስነታቸውና ታሪካዊነታቸው ለአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ኢንስቲትዩትና ለ10 ክፍለ ከተሞች ቢበተንም በየእለቱ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል ብለዋል፡፡

መንግሥት ብዙ ሚሊየን ብር በጀቶና መድቦ በቅርቡ ምዝገባና እድሣት ማካሄዱ ይታወሣል፡፡

ስለ ታሪካዊነታቸው ለደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ተናግረን ከመፍረስ እንዲታደግ ብንጠይቅም በአዳዲስ ህገ-ወጥ ግንባታዎች ጉዳይ እንጂ በአሮጌ ቤት ፈረሳ አያገባኝም የሚል ምላሽ ሰጥቶናል ብለዋል፡፡

አቶ አበበ በተለይ ከወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች ጋር መግባባት አቅቶናል፤ አሮጌ ቤቶችን የሚገዙ ባለሃብቶች ቤቶቹን ገዝተው ውዝግብ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ከቢሮው ጋር መነጋገር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

Advertisement