NEWS: ኳታር የ80 ሀገራት ዜጎች ያለቪዛ ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ ፈቀደች::

                                                         

ኳታር ከ80 በላይ ሀገራት ዜጎች ከቪዛ ነጻ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡበትን መርሃ ግብር ይፋ ማድረጓን አስታወቀች።

ዶሃ በባህረ ሰላጤው ጎረቤት ሀገራት በደረሰባት መገለል በአየር ትራንስፖርት እና ቱሪዝም የተፈጠረውን ቀውስ ለማነቃቃት መርሃ ግብሩን ይፋ ማድረጓን የኳታር የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአዲሱ አሰራር የአውሮፓ ሀገራት ዜጎች፣ ህንዳውያን፣ ሊባኖሳውያን፣ ኒውዝላንዳውያን፣ ደቡብ አፍሪካውያን እና አሜሪካውያንን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ዜጎች የይለፍ መታወቂያ ብቻ በማሳየት ወደ ኳታር መግባት ይችላሉ ነው የተባለው፡፡

የ33 ሀገራት ዜጎች በኳታር ለ180 ቀናት ያለቪዛ መቆየት የሚችሉ ሲሆን የ47 ሀገራት ዜጎች ደግሞ ለ30 ቀናት መቆየት እንደሚችሉ አስታውቃለች፡፡

በኳታር የቱሪዝም መስሪያ ቤት የቱሪዝም ልማት ከፍተኛ ኦፊሰሩ ሀሰን አል ኢብራሂም፥ ዶሃ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ያለ ቪዛ እንዲገቡ መፍቀዷ በቀጠናው ለጎብኝዎች በሯን ክፍት ያደረገች ሀገር የመሆኗ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅ፣ ባህሬን እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ ባለፈው ሰኔ ወር ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በሚል ከኳታር ጋር የነበራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸው ይታወሳል፡፡

ዶሃ ውንጀላውን ብታጣጥለውም በሳዑዲ የሚመሩት አራቱ ሀገራት ከኳታር ጋር ያላቸውን ሁሉንም የትራንስፖርት ግንኙነት ሰርዘው ነበር፡፡
በዚህም የሀገሪቱ አለኝታ የሆነው ኳታር ኤር ዌይስ በረራዎች በመስተጓጎላቸው ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

በጎረቤቶቿ መገለል የደረሰባት ዶሃ የንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲቀጥል ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡

የሌሎች ሀገራት ዜጎች ያለ ቪዛ ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ መፍቀዷ በረዥም ጊዜ እቅድ ነጻ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያየዘችው ግብ ማሳኪያ ተደርጎ ይቆጠራል ነው የተባለው፡፡

ኳታር አሁን ላይ የምግብ አቅርቦቶችን ከቱርክ እና ከኢራን የምታስገባ ሲሆን የግንባታ ግብዓቶችን ደግሞ በኦማን የባህር መስመር እያስመጣች ትገኛለች፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement