NEWS: ሰሜን ኮሪያ ወደ አሜሪካዋ ጉዋም አራት ሚሳኤሎችን ለማስወንጨፍ አቅዳለች

                                

ሰሜን ኮሪያ በምዕራባዊ ፓስፊክ ጉዋም በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ አቅራቢያ አራት ሚሳኤሎችን ለማስወንጨፍ የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀቷ ተገልጿል።

የሀገሪቱ ብሄራዊ የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገበው እቅዱ በኪም ጆንግ ኡን ከፀደቀ Hwasong-12 የተሰኘው ሚሳኤል በጃፓን ሰማይ ላይ አልፎ ከጉዋም 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በባህር ውስጥ የሚያርፍ ይሆናል።

እቅዱ ፒዮንግያንግ የዶናልድ ትራምፕን ማስጠንቀቂያ ከቁብ እንደማትቆጥረው ያሳየ መሆኑም ነው የተገለፀው።

ሰሜን ኮሪያ እየፈፀመችው ያለው ተግባር “የአገዛዙ (የኪም ጆንግ ኡን) ማክተሚያ” ነው ስትል ዋሽንግተን ማስጠንቀቋ ይታወሳል።

የሀገሪቱ መከላከያ ሀይል ይህን እቅዱን እስከ ነሃሴ ወር አጋማሽ አጠናቆ ለኪም ጆንግ ኡን እንደሚያቀርብም ተዘግቧል።

“Hwasong-12” በጃፓኖቹ ሺማነ፣ ሂሮሺማ እና ኪዮቺ ግዛት ሰማይ ላይ የሚያልፍ ሲሆን፥ ለ17 ደቂቃዎች 1 ሺህ 3 ሺህ 356 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ ከጉዋም 30 ወይንም 40 ኪሎ ሜትር ርቆ በውሃማ አካል ውስጥ ያርፋል ብለዋል የሰሜን ኮሪያ ጦር አዛዥ ጀነራል ኪም ራክ ግዮም።

“Hwasong” በሰሜን ኮሪያ በሀገር ውስጥ የተመረተ መካከለኛ እና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ነው።

ፒዮንግያንግ ሚሳኤል ልትሞክርባት እቅድ ያወጣችባት የአሜሪካዋ ጉዋም ደሴት የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ ማዕከል ስትሆን 163 ሺህ ነዋሪዎች አሏት።

የግዛቷ ሩብ ክፍልም በአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ የተያዘ ሲሆን፥ ከ6 ሺህ በላይ ወታደሮች ሰፍረውባታል።

541 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ጉዋም በፊሊፒንስ እና ሃዋይ መካከል የምትገኝ ደሴት ናት።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው እለት የዋሽንግተን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ከወትሮው የበለጠ ሀይል እንዳለው ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቲለርሰንም ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ ስጋት እንደማትሆን ለአሜሪካውያን በድጋሚ አረጋግጠውላቸዋል።

በጉዋም ጉብኝት ያደረጉት ቲለርሰን ሩስያ እና ቻይናን ጨምሮ አለም አቀፉ ማህበረሰብ እያደረገው ያለው ግፊት ከፒዮንግያንግ ጋር አዲስ ድርድር ለመጀመር እንደሚያስችልም ተስፋ አለኝ ብለዋል።

የደቡብ ኮሪያ መከላከያ አዲሱን የሰሜን ኮሪያ እቅድ ከወትሮው ያልተለየ ነው፤ ፀብ አጫሪነት ነው ብሏል።

ቻይና በበኩሏ ሁኔታውን “ውስብስብ እና ስሜታዊ” ስትል ገልፃዋለች።

ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግስታትን ማዕቀብ ወደ ጎን በመተው ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ሁለት የኒዩክሌር ሙከራዎችን ያደረገች ሲሆን ባለፈው ሀምሌ ወርም ሁለት አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ማከናወኗ ይታወሳል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement