በብቸኝነት እንዴት መኖር ይችላሉ?

ይብዛም ይነስ የሰው ልጅ በህይዎት እያለ የብቸኝነት ስሜት ማስተናገዱና የተወሰኑ ጊዜያቶችንም በብቸኝነት ማሳለፉ አይቀሬ ነው።

ከቤተሰብ ተነጥሎ ለስራ አልያም በሌላ አጋጣሚ ከቤተሰብ መራቅ፣ ከአብሮ አደግና ከልጅነት ጓደኛ በህይዎት አጋጣሚ መነጠልና መለየት እንዲሁም መሰል አጋጣሚዎች ለብቸኝነት ሊዳርጉ ይችላሉ።

የስነ ልቦና ባለሙያዎችም ብቸኝነት የሰው ልጅ አንዱ የህይዎት ገጽታ የመሆን አጋጣሚው የሰፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን አጋጣሚ መቀበልና መላመድ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

ከዚህ አንጻርም አጋጣሚው እስከሚገኝ ድረስ ብቸኝነትን ከመጋፋት አምኖና ተቀብሎ መኖርን ይመክራሉ።

ከብቸኝነት ጋር አብሮ ለመኖርና ስሜቱን ለመቀበል ደግሞ የሚከተሉትን መንገዶች ይጠቅሳሉ፤

የአጭር ጊዜ መፍትሄ አለመውሰድና ራስን ማሳመን፦ አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነትን ለማምለጥና የአጭር ጊዜ መፍትሄ ከመፈለግ አንጻር አላስፈላጊ ስሜት ውስጥ በመግባት የማይጠቅሙ እርምጃዎችን መውሰድ ይስተዋላል።

አብዝቶ መጠጣትና ራስን በዚያ አጋጣሚ የመደበቅ አዝማሚያዎች ደግሞ በዚህ ወቅት የሚስተዋሉ አጋጣሚዎች ናቸው።

ይህ ግን ራስን ለከፋ ጉዳት ከመዳረግና ከመሸነፍ ውጭ ሌላ መፍትሄ አያመጣም፥ ከዚያ ይልቅ የአጭር ጊዜ መፍትሄውን በመተው ያንን ህይዎት መላመድና ራስን ማሳመኑ መልካም ነው።

የሚኖሩትን ህይዎት አምነው በመቀበል ወደውት ሲኖሩት ዘለቄታዊ ደስታና የአዕምሮ እረፍትም ያገኛሉና ነገሩን አምኖ መቀበልና መላመድን ይምረጡ።

ባይመችዎትም እስካሉ ድረስ አምኖ መቀበል ከራስም ሆነ ኬሎች ጋር ተስማምቶና ተግባብቶ ለመኖር ቁልፉ ነውና ይጠቀሙበት።

አጋጣሚውን መጋፈጥ፦ በልጅነት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በሌሎች ላይ በተለይም ቤተሰብ ላይ የተመሰረተና የተወሰነ ነበር።

በዚያ ወቅት ለመመገብ፣ ለመጠጣትና ለመጫዎትም ሆነ ለመዝናናት የሌሎችን እርዳታ መሻትና መጠበቅ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

ባለሙያዎቹ በልጅነት ዘመን የሚሰማ ብቸኝነት በወጣትነት ዘመን በህይዎት አጋጣሚ ከቤተሰብ ሲለዩ ሊከሰት እንደሚችል ያነሳሉ።

በዚህ ወቅት ከቤተሰብ፣ ከፍቅረኛ፣ ከቅርብ ጓደኛና ወዳጅ ጋር ሊራራቁ እና በልጅነት ጊዜ ይሰማዎት የነበረው የብቸኝነት ስሜት ተመልሶ ሊመጣና ብቸኛ እንደሆኑም ሊያስቡ ይችላሉ።

ይህ ግን ብቸኝነትን ከመፍራትና በቤተሰብና ጓደኛ ተከቦ መኖርን ከመፈለግ የመነጨ እንጅ ያን ያክል አስጨናቂና አስፈሪ አጋጣሚ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

በዚህ ወቅት እንደ ልጅነት ጊዜ ማሰብ ሳይሆን እንደ ትልቅ ሰው በርካታ አማራጮች እንዳሉ ማሰብና ራስዎን እንደቻሉ ማስታወስም ይገባወታል።

ከዚህ አንጻርም እንደልጅነት ዘመን ብቻየን ነኝና ድረሱልኝ ሳይሆን፥ ብቸኝነትዎን መላመድና በምን መልኩ ህይወቴን መምራት አለብኝ በማለት ፈተናውን ለመወጣት መዘጋጀት ይኖርብዎታል።

ለምን ብሎ አለመጠየቅ፦ አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ብቸኛ ሆነው ሲያገኙት፤ ለምን ብቸኛ ሆንኩ? እና ለምን የብቸኝነት ስሜት ይሰማኛል? የሚል ጥያቄ ራሳቸውን ይጠይቃሉ።

አንድ ነገር ከሆነ በኋላ ለምን የሚል ጥያቄ ራስን መጠየቅ ግን መፍትሄ ማግኛ መንገዶችን የሚያጠብበት አጋጣሚ ሰፊ ስለመሆኑም ይነገራል።

ለምን ብለው መጠየቅ ሲጀምሩ ራስን መውቀስና አላስፈላጊ ቁጭት ውስጥ የመግባት አጋጣሚዎም የሰፋ ይሆናል።

ለምን የሚል ጥያቄን በደጋሙ ቁጥርም ለነገሮች ወሰን በማበጀት ሰፋ ያለውን አማራጭ እንዳያስተውሉም ያግድዎታል፤ ከዚህ ባለፈም ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ነገሮችን ፍለጋ ላይ እንዲያተኩሩም ሊያደርግዎት ይችላል።

ይህን ጥያቄ በጠየቁ ቁጥርም የከፋ ስሜትን እንዲሰማዎት በማድረግ ነገሩን ከመቀበል ወደ መቃወም እንዲያመሩና ምናልባት መፍትሄ አልባ ያደርግዎታል።

ከዚያ ይልቅ ምን ተፈጠረ? ከሆነው ነገር ምንስ አገኘሁ? በቀጣይስ ምን ያጋጥመኛል? ብሎ መጠየቁን የተሻለ መሆኑንም ነው ባለሙያዎች የሚመክሩት።

ምክንያቱም ይህን ሲጠይቁ ለችግሩም ሆነ ለጠየቁት ነገር አዳዲስ ነገሮች በማግኘት ሰፋ ያሉ እይታዎች እንዲኖርዎት ያግዛልና።

ስሜቱን እንደ ህይዎትዎ አንድ ክፍል መቀበል፦ ሁልጊዜም ቢሆን ህይዎት ላይ የሚከሰቱ ለውጦች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ለብቸኝነት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው።

ከዚህ ቀደም የለመዱትን ህይዎት በመተው አዲስ ህይዎትን ለመጀመር ሲያስቡ ጀምሮ የብቸኝነት ስሜት ይከሰታል።

አዲስ የሚገጥምዎትን ህይዎትና የአካባቢውን አጠቃላይ ሁኔታ ለማወቅ ከመጨነቅ አንጻር ለብቸኝነት ስሜት መዳረግዎም አይቀርም።

እንዲህ ባለ ስሜት ራስን ማስጨነቅና ባልተገባ ስሜት ውስጥ መቆየቱ ግን ብዙም አስፈላጊ አይደለም፥ ከዚያ ይልቅ አጋጣሚውን የህይዎት አካል አድርጎ ማስቀጠል የተሻለው አማራጭ ነው።

ዘወትር ህይዎትዎን በተለያዩ አቅጣጫዎች እንደሚመሩ ማሰቡም መልካም መሆኑን ያስረዳሉ የስነ ልቦና ባለሙያዎች።

የመጣውን አምኖ መቀበል በሄዱበት ሁሉ ምቹ ከባቢን ለመፍጠርም ያግዛልና በዚያ መልኩ ህይዎትዎን ለመምራት ይሞክሩ።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ብቸኝነትን ከፍቅረኛዎም ቢለዩ እንኳን ሁኔታው የተለመደ እንደሆነ በማሰብ መቀበል ይገባዎታል።

የመለየት ስሜት አንዳንድ ጊዜም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የሚመጣና ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚም ስላለ፥ ይህን አጋጣሚ ቀለል አድርጎ ማየትን መልመዱ መልካም መሆኑን ነው የስነ ልቦና ባለሙያዎች የሚያነሱት።

በዚህ ወቅት ራስን ማግለል ሳይሆን በአካባቢዎ ካለ ማህበረሰብ ጋር መቀራረብ።

ከወዳጅዎ ርቀው ሰው ሲቀርቡም የተፈጠረብዎትን ብቸኝነት መራቂያና መደበቂያ ለማድረግ ሳይሆን፥ ሰዎኛ ባህሪ ከመሆኑ አንጻር በብቸኝነት እንዳይጎዱ መሆን አለበት።

ይህን መሰሉ ማህበራዊ መስተጋብር ዘወትር ብቸኛ ነኝ እያሉ የፍቅረኛዎን እገዛ ሳይጠብቁና ሳይፈልጉ ተራርቀውም ቢሆን መኖር መቻልዎን ማሳያ ነው።

ሁሉም ብቸኝነት እንደሚሰማው ያስቡ፦ ይብዛም ይነስ ሁሉም ሰው የብቸኝነት ስሜት እንደሚሰማው ማስታወስ ይኖርብዎታል።

በብቸኝነት ስሜት ብቻዎን እንዳልሆኑ ማሰብ ሲጀምሩ፥ በዚህ ስሜት እንደተጎዱ በማሰብ ራስዎን ከማህበረሰቡ የማግለል ስሜትዎ እንዲቀንስና ከሌሎች ጋር እንዲተሳሰሩ ይረዳወታል።

በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት መጠኑ ይለያይ እንጅ አብዛኛው የሰው ልጅ በርካታ የሚጋራቸው ስሜቶች እንዳሉት ማስታወስም ይገባል።

ይህ ደግሞ ለአብሮነትና ለአንድነት ስሜቱ መልካም ነውና ብቻየን አይደለሁም ብለው ያስቡ፤ ያንኑ ህይዎትም ይኑሩት።

በዚህ ስሜት የተጠቁ ከሆነና ምናልባት ከተቸገሩ በአካባቢዎ በሚገኙ የማህበረሰብ አቀፍና መሰል ማህበራት ጎራ በማለት ከሰዎች ጋር ይገናኙ።

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement