NEWS: ብሪታንያ ስማርት ተሽከርካሪዎችን ከመረጃ ጠላፊዎች ለመጠበቅ የሚያግዝ መመሪያ አወጣች::

                                   

ብሪታንያ መንግስት አሽከርካሪ አልባ እና ከኢንተርኔት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተሽከርካሪዎች የሚያመርቱ ድርጅቶች ተሽከርካሪዎቹ ለመረጃ ጠላፊዎች እንዳይጋለጡ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ስርአት እንዲዘረጉ የሚጠይቅ መመሪያ አውጥቷል።

አሽከርካሪዎች ካርታ እና የጉዞ መረጃዎችን በኢንተርኔት ግንኙነት እንዲያገኙ የሚያስችሉት ስማርት ተሽከርካሪዎች የመረጃ መንታፊዎች ኢላማ ሊደረጉ እንደሚችሉም ነው ለንደን ያስታወቀችው።

አምራቾች ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ስርአት ካልዘረጉ የመረጃ ጠላፊዎች የስማርት ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎችን የግል መረጃ በቀላሉ ሊወስዱ ይችላሉ፤ ያለቁልፍ የሚከፈቱ ተሽከርካሪዎችን ሊዘርፉና የተለያዩ ቫይረሶችን በማሰራጨት ተሽከርካሪዎቹን በቁጥጥራቸው ስር ሊያውሉ እንደሚችሉም ነው የተገለፀው።

አዲሱ መመሪያ የመኪና አምራች መሃንዲሶች አዲስ ተሽከርካሪ ሲያመርቱ የሳይበር ደህንነት ስጋቱንም ጭምር አብረው እንዲሰሩ ያስገድዷል ብሏል የብሪታንያ መንግስት።

የሀገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ማርቲን ካላናን እንደሚሉት፥ ስማርት ተሽከርካሪዎች ከተለያዩ የገመድ አልባ ኢንተርኔት (ዋይፋይ) መስመሮች ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ በመሆኑ ከሳይበር ጥቃቶች ሊጠበቁ ይገባል።

መመሪያው ወደ ተሽከርካሪዎቹ የሚላኩ የተሳሳቱ አልያም በካይ ቫይረሶችን የያዙ ትዕዛዞችን የሚቆጣጠር ስርአት አምራች ድርጅቶቹ እንዲዘረጉ ይጠይቃል።

ተጠቃሚዎችም በተሽከርካሪዎቹ የሚቀር የግል መረጃቸውን እንዲያጠፉ የሚፈቅድ አሰራር እንዲኖር መመሪያው ያስገድዳል።

አምራቾች ለረጅም አመታት የተሽከርካሪዎቹን የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅ ከደንበኞቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ዙሪያም እቅድ ሊኖራቸው ይገባል ይላል።

ከዚህም በተጨማሪ የብሪታንያ መንግስት አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች መድህን እንዲገባላቸው አዲስ ህግ እያዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

ለአሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች መድህን ይገባላቸው የሚለው ሀሳብ በመድህን ሰጪ ተቋማት እና ህግ አስፈፃሚዎች መካከል ልዩነት ፈጥሯል።

ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ ተሽከርካሪዎች አደጋ ቢደርስባቸው ለአደጋው ሀላፊነቱን የሚወስደው አካል ማን ነው የሚለው ነው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement