NEWS: በ10 አመቷ ተደፍራ ያረገዘችው ህንዳዊ ፅንሱን እንዳታቋርጥ በፍርድ ቤት ታግዳለች

                                       

በሰሜናዊ ህንድ ቻንዲጋርህ ግዛት በ10 አመቷ ተደፍራ ያረገዘችው ታዳጊ ፅንሷን እንዳታቋርጥ በፍርድ ቤት መወሰኑ በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዋነኛ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል።

የቢቢሲው ዘጋቢ ጊታ ፓንዴይ ወደ አካባቢው አምርቶ ያናገራቸው የግዛቷ የህግ አገልግሎት ባለሙያ ማሃቪር ሲንግ፥ “ከ14 እስከ 15 አመት ባለ እድሜያቸው የሚያረግዙ በርካታ ታዳጊዎች ቢኖሩም በ10 አመቷ ያረገዘች ልጅ ግን ስመለከት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜዬ ነው” ብለዋል። 

በታዳጊዋ ላይ ተደጋጋሚ የወሲብ ትንኮሳ ይፈፀምባት የነበረው የወላጆቿ ቤተሰብም በአሁኑ ወቅት ማረሚያ ቤት ይገኛል።

ደስተኛ እና ሳቂታዋ ታዳጊ አይናፋርና ከሰዎች ጋር ማውራት ብዙም የማትደፍር ናት ተብሏል።

ስሟ ያልተጠቀሰው የ6ኛ ክፍል ተማሪ ስዕል፣ የእንግሊዝኛ እና ሂሳብ ትምህርቶችን እንደምትወድም ነው የተነገረው።

በህንድ ህግ የእናቲቱ ህይወት አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል የሀኪሞች ማረጋገጫ እስካልቀረበ ድረስ ከ20 ሳምንታት በላይ የቆየ ፅንስን ማቋረጥ አይፈቅድም።

ይሁን እንጂ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአስገድዶ መድፈር ምክንያት የሚያረግዙ በርካታ ታዳጊዎች ከፀነሱ ከ20 ሳምንታት በላይ እድሜ ያለው ፅንስ እንዲቋረጥ ለፍርድ ቤት አቤቱታቸውን እያቀረቡ ነው።

ታዳጊዎቹ እድሜያቸው ለጋ ከመሆኑ አንፃር መፀነሳቸውን የሚያውቁት በጣም ዘግይተው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው ህጉ እንዲሻሻል በርካቶች የሚጠይቁት።

የ10 አመቷ ታዳጊ መፀነሷ የታወቀውም ከሶስት ሳምንት በፊት ነው።

በታችኛው ሆዷ በኩል የህመም ስሜት እንደሚሰማት ከተናገረች በኋላ እናቷ ወደ ህክምና ተቋም ከወሰዷት በኋላ ማርገዟ መረጋገጡም ነው የተነገረው።

የታዳጊዋ ቤተሰቦችም ሆኑ ጓደኛዋ በሀኪሞች እስኪረጋገጥ ድረስ ምንም አይነት የህመም ምልክት እንዳላዩባት ተናግረዋል።

ታዳጊዋ እስካሁን በማህፀኗ ልጅ መፀነሷ ሳይሆን በሆዷ ውስጥ ትልቅ ድንጋይ እንዳለ እና ሆዷ ያበጠውም በዚሁ ምክንያት መሆኑ ነው የተነገራት።

ሰሞኑን ፖሊሶች፣ አማካሪዎች እና ጋዜጠኞች በታዳጊዋ ቤተሰቦች ቤት አካባቢ መበራከታቸው ግን ምናልባትም ጥርጣሬ ውስጥ እንድትገባ ሳያደርጋት አይቀርም ተብሏል።

ታዳጊዋ በአሁኑ ወቅት በልዩ መልኩ እንቁላል፣ ወተት፣ ፍራፍሬ፣ አሳ እና ዶሮ እንድትመገብ እየተደረገ ነው።

የታዳጊዋ ወላጆች ባለፈው ሳምንት ታዳጊዋን ወክለው ፅንሱ እንዲቋረጥ ለህንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደርጓል።

ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ታዳጊዋ ከፀነሰች 32 ሳምንታት የተቆጠረ መሆኑና ዶክተሮች የፅንስ መቋረጡ ለታዳጊዋ ህይወት አደገኛ መሆኑን መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ የታዳጊዋ ቤተሰቦች ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቷቸዋል።

የታዳጊዋን የመደፈር ወንጀል እየመረመሩ ያሉት ፖሊስ ፕራቲሃ ኩማሪ፥ የታዳጊዋ ወላጆች በጣም ምስኪን መሆናቸውንና እናቷ ከማልቀስ ውጭ የሚናገሩት ነገር እንደሌላቸው ገልፀዋል።

አባቷም ልጃቸው የተገደለች ያህን እንደሚሰማቸው መናገራቸውንም ነው የጠቆሙት።

በህንድ በየ155 ደቂቃው አንዲት ከ16 አመት በታች የሆነች ታዳጊ ትደፈራለች፤ በየ13 ስአቱ ደግሞ አንዲት ከ10 አመት በታች ህፃን የአስገድዶ መደፈር ይደርስባታል። 

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ከ10 ሺህ በላይ ህፃናት በህንድ በሀይል ተደፍረዋል።

240 ሚሊየን ህንዳውያን ሴቶች እድሜያቸው 18 አመት ሳይሞላ ጋብቻ ይፈፅማሉ።

የህንድ መንግስት ባደረገው ጥናት 53 ነጥብ 22 በመቶ ህንዳውያን ህፃናት የተለያየ ወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸው ተረጋግጧል።

50 በመቶ ጥቃት አድራሾቹም በህፃናቱ ዘንድ የሚታወቁ እና ህፃናቱን የሚንከባከቡ ናቸው።

በህንድ በየአመቱ 45 ሺህ ወጣት ሴቶች በወሊድ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል።

ምንጭ፦ የህንድ መንግስት እና ዩኒሴፍ

የታዳጊዋ አባት ጋዜጠኞች ቤታቸው አካባቢ አለመጥፋታቸው እና የልጃቸውን አንገብጋቢ ጉዳይ ለገበያ ፍጆታቸው እያዋሉት መሆኑ እንዳበሳጫቸው ገልፀዋል።

የባለቤታቸው የአጎት ልጅ ታዳጊዋን መድፈሩን ማመኑን የተናገሩት አባቷ፥ ከበድ ያለ ቅጣት እንዲጣልበትና በማረሚያ ቤት እድሜውን እንዲጨርስ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።

ታዳጊዋ ሊገጥማት የሚችለው የጤና እክል እና ስታድግ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚፈጠርባት መገለል ወላጆቿን ከአሁኑ እያስጨነቀ ነው።

የህክምና ምርመራዎች እስካሁን የታዳጊዋ ጤና “መልካም” መሆኑን ቢያሳዩም በደሟ ውስጥ ከፍተኛ የቀይ ህዋስ ወይም ሄሞግሎቢን እጥረት ሊያጋጥማት እንደሚችል ተጠቅሷል።

የህንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፅንሱ ይቀጥል በሚለው ውሳኔው በመፅናቱ የ10 አመቷ ታዳጊ በመጪው መስከረም ወር በቀዶ ህክምና እንድትወልድ ይደረጋል ተብሏል።

“የ10 አመት ህፃን እንዴት መውለድ ትችላለች? ለህይወቷስ አደገኛ አይሆንም ወይ? የሚሉ የህፃናት መብት ተሟጋቾችም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ዘመቻ ከፍተዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement