NEWS: በመዲናዋ የመኖሪያ ቤቶችን በማህበር መገንባት የሚያስችል ጥናት ተጠናቋል

                                                                

በትዕግስት አበርሃም

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣይ ዓመት በህብረት ስራ ማህበራት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ጥናት አጠናቆ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በጥናቱ እነማን በምን መልኩ በህብረት ስራ ማህበራት መሰተፍ ይችላሉ የሚለውን ጨምሮ የቀድሞውን መመሪያ የማሻሻል እና በሌሎች ጉዳዮች ውይይት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅሷል፡፡

በሚኒስቴሩ የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ታደሰ ገብረጊዮርጊስ እንዳሉት፥ ከዚህ ቀደም በህብረት ስራ ማህበራት ላይ ያለው ፍላጎት አናሳ ስለነበር፥ አዲስ አበባ ላይ በማህበር ተደራጅተው ወደ ግንባታ የገቡ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው።

በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ፍላጎት በማደጉ የከተማዋ አስተዳደር ይህን አሰራር ለመተግበር የሚያስችል ጥናት አጠናቆ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል ነው ያሉት ሀላፊው።

በተለይም በዚህ አሰራር የተሻለ አፈጻጸም ያለውን የትግራይ ክልልን ተሞኩሮ ወደ አዲስ አበባ የማምጣቱ ጉዳይ የውይይቱ አካል ነው።

በሌላ በኩል በ20/80 መርሃ ግብር ላይ እየተገነቡ ያሉ ከ52 ሺህ በላይ የጋራ መኖርያ ቤቶች ግንባታን በ2010 ዓ.ም ወይም በ2011 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡

አሁን በግንባታ ላይ ካሉት ቤቶችም 26 ሺህ ያህሉ አፈጻጸማቸው ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ግንባታቸው ሲጠናቀቅም በ1997 ተመዝግበው እየተጠባበቁ ያሉ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ባለእድል እንደሚሆኑ ነው የጠቆሙት።

የመሰረተ ልማት ሙሉ ለሙሉ ሳይሟላላቸው የሚተላለፉ ቤቶች ጉዳይ ነዋሪዎችን ለብዙ አይነት ምሬት እያጋለጣቸው ነው።

የቢሮው ሀላፊ አቶ ታደሰ ግን ችግሩ ቤቶችን በፍጥነት ለማስተለለፍ ከሚደረገው ጥረት ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement