ሁለገቡ የሞያ ባለቤት ተስፋዬ ሣኅሉ (አባባ ተስፋዬ) ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የ96 ዓመቱ አባባ ተስፋዬ በዕድሜ ምክኒያት በመጣ ሕመም እቤት ውስጥ ከዋሉ ወራት መቆጠሩን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ። እስከ ትናንት ድረስ ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በደንብ ሲነጋገሩና ሲጨዋወቱ ቆይተው ዛሬ ከቀኑ ሰባት ሰዓት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉን ገልፀውልናል።

ቤተሰቦቻቸው ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት ቅዳሜ ዕለት ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በሕይወት ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋፆ የክብር ዶክትሬት እንደሰጣቸውና እሱን ሽልማት ተቀብላ ስትሰጣቸው በጣም ተደስተው እንደነበር ገልፃልናለች።
አባባ ተሰፋዬ በወጣትነት ዕድሜያቸው የመድረክ ተዋናይ፣ ድምፃዊ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ የልጆች የተረት መፅሐፍ አዘጋጅና፣የምትሃት ባለሞያ በመሆን በዘርፈ ብዙ ሞያ አገልግለዋል። ከሥራቸው ውስጥም በትውልድ ውስጥ ተቀርፀው የቀሩበት አገለግሎታቸው ከ1957 ጀምሮ ለ40 ዓመታት ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ፕሮግራም ነው።
የአባባ ተስፋዬ የቀብር ሥነ ሥርዓት መቼና የት እንደሚፈፀም ገና አለመወሰኑን ቤተሰቦቻቸው ገልፀውልናል። 

ምንጭ ፥ ቪ ኦ ኤ (VOA)

Advertisement