NEWS: ቻይና ለመረጃ መረብ ስጋት የሆነ ቫይረስ አሰራጭተዋል ያለቻቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አዋለች::

                                               

የቻይና ፖሊስ የመረጃ መረብን ለመጥለፍ የሚውል ቫይረስ አሰራጭተዋል ያላቸውን ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።

የሃገሪቱ ፖሊስ እንዳስታወቀው በቁጥጥር ስር ግለሰቦች፥ መቀመጫውን ቤጂንግ ያደረገ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ሰራተኞች ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ ለበርካታ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች መጥፋት ምክንያት ነው የተባለ አደገኛ ቫይረስ በመስራት አሰራጭተዋል በሚል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ተጠርጣሪዎቹ ለኩባንያው ፋየር ቦል የተሰኘ የኮምፒውተር ቫይረሰን አምርተዋል።

እንደ ፖሊስ መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ ያመረቱትን ቫይረስ ከቻይና ውጭ ባሉ ሃገራት አሰራጭተዋል።

ቫይረሱም ታዲያም ከቻይና ውጭ የሚገኙ ግዙፍ ተቋማትን የኮምፒውተር እና መረጃ መረብ ላይ ጉዳት አድርሷል ነው የተባለው።

በቫይረሱ ሳቢያም በአንድ አመት ብቻ ከ250 ሚሊየን በላይ ኮምፒውተሮች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል ተብሏል።

ይህን ተከትሎም የሃገሪቱ ፖሊስ በዚህ ቫይረስ ማምረትና ስርጭት ስራ ላይ ዋነኛ ተዋናይ ናቸው ያላቸውን ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሏል።

ተጠርጣሪዎቹ ቫይረሱን ከተለያዩ የመረጃ አድራሻዎች ጋር በማጣመር ሲለቁት ነበር በሚል ፖሊስ ግምቱን ገልጿል።

ኩባንያው በዚህ መልኩ አምርቶታል የተባለው ቫይረስ ታዲያ ኮምፒውተሮች ላይ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ ለተቋሙም የገቢ ምንጭ ሆኗል።

ወጣቶቹ የኩባንያው ሰራተኞች 11 ነጥብ 85 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በዚህ ቫይረስ ብቻ ማስገባታቸው ተገልጿል።

ከመረጃ መረብ ጥቃት ጋር በተያያዘ ቻይና በተለይም በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብባት ቆይቷል።

ሁለቱ አካላት መቀመጫቸውን ቻይና ያደረጉ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የተለያዩ ሃገራትን መረጃዎች ለመመዝበር የሚውሉ ቫይረሶችን ያመርታሉ በሚል ውንጀላ ሲያቀርቡም ነበር።

ቤጂንግ በበኩሏ የሚቀርብባትን ውንጀላ በተደጋጋሚ ስታስተባብል ቆይታለች።

የአሁኑ የቤጂንግ እርምጃ ምናልባትም ሃገሪቱ በምታወራው ልክ የመረጃ መረብ ደህንነት ስጋትን ለመቀነስ ከሃገራት ጋር ተባብራ ለመስራት ያላትን ዝግጁነት ማሳያ ሊሆን ይችላልም ተብሏል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement