በስራ ቦታ የሚያጋጥምን ከፍተኛ ጭንቀት በ10 ደቂቃ ውስጥ ሊያስወግዱ የሚችሉ 10 ተግባራት

                                                             

በዚህ ዘመን በርካታ ሰዎች ለጭንቀት እንደሚጋለጡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ከፍተኛ ጭንቀት እና ትካዜ ወደ አዕምሯችን በሚመጡ የግል ወይም ማህበራዊ ችግሮች ሊከሰት ይችላል፡፡

የዋተርሉ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በዚህ ዓመት በቢሮ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉና ለጭንቀት የሚዳረጉ በርካታ ሰዎችን ጠይቀው በሰሩት ጥናት ካጋጠማቸው መጥፎ ስሜት ለመራቅ በርካታ ተግባራትን እንደሚከያናውኑ ጠቅሰዋል፡፡

በቢሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ የስራ ጭንቀቶችን በ10 ደቂቃ ውስጥ ለማስወገድ የሚጠቅሙ 10 ተግባራትን እነሆ ብሏል ጥናቱ፡፡

1. ስዕል መሞከር

የዋተርሉ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደሚመክሩት ከሆነ በቢሮ ውስጥ ከፍተኛ ጭንቀት በሚያጋጥመን ጊዜ ወረቀት እና እርሳስን በማገናኘት ስለሚያስጨንቀን ነገር ለመሳል ብንሞከር ተመራጭ ነው፡፡

በአንጎል ውስጥ የሚገኘው ጭንቀት፣ ትካዜ እና ፍርሃት በምስል ሲታይ ቀለል ይለናል ይላሉ ተመራማሪዎች፡፡

2. ጭንቀት እና ውጥረትን ለመቀነስ የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም

በበለፀጉት ሀገራት ዜጎችን ከጭንቀት እና ከድብርት የሚያወጡ በርካታ መተግበሪያዎች ተሰርተው ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ መተግበሪዎች ከፍተኛ ጭንቀትን እንዴት ማስወገድ እንደሚገባ በማስገንዘብ እና ለራስ መልካም ነገርን ማሰብ ያለውን ጥቅም በማሳወቅ በርካቶችን ታድገዋል፡፡

3. ከፍተኛ ጭንቀት ሲያጋጥም አንድ ብርጭቆ ውሃ መጠጣት

በአዕምሮ ውስጥ ያለው የጭንቀት ነበልባል ቀዝቀዝ እንዲል በአንድ ትንፋሽ አንድ የብርጭቆ ውሃን መጠጣት ይመከራል፡፡

በተለይም እስትንፋስ መረጋጋትን እና የሰውነት መሞቅን እንዲሁም የአዕምሮ መወጠርን ለማርገብ ጥቅሙ ላቅ ያለ ነው ተብሏል፡፡

4. የሚወዱትን ዜማ ወይም ሙዚቃ ማዳመጥ

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሙዚቃ ሕይወቴ ይላሉ፤ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ደግሞ በስራ ቦታ ላይ ለሚያጋጥም ጭንቀት የሚወዱትን ሙዚቃ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ማዳመጥ መፍትሔ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ለአብነትም ወከባ በሚበዛበት ቢሮ ውስጥ ሆነው በግል የጆሮ ማዳመጫዎ አይንዎን ጨፍነው ሙዚቃ ወይም መዝሙርን ለአምስት ደቂቃ ቢያዳምጡ ትካዜ እና ጭንቀት ከአዕምሮ እንዲርቅ ያደርጋል ተብሏል፡፡

በተለይም ለተመስጦ የሚረዱ ሙዚቃዎችን ማዳመጥ መልካም መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

5. የእንቆቅልሽ ይዘት ያላቸውን ጨዋታዎች መጫዎት

ብዙ ጊዜ እንቆቅልሽ የልጆችን አዕምሮ ለማጎልበት አካባቢያዊ ነገሮችን መነሻ በማድረግ በጥያቄና መልስ መልኩ አዝናኝ ሆኖ ይቀርባል፡፡

ይህ ልምድ በስራ ቦታ ቢተገበር ሰዎች የሚጋጥማቸውን ጭንቀትና ትካዜ ለመቅረፍ ወሳኝ ነው፡፡

በተለይም በቢሮ ውስጥ በጠጴዛችን ላይ በቀላሉ በተዘጋጁ ቅርጾች ላይ ቃላትን፣ ቁጥሮችን ወይም የተቆራረጡ ምስሎችን በማገጣጠም መጫወት ከፍተኛ የሆነውን የአዕምሮ ጭንቀት ከ10 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማስወገድ ያግዛል፡፡

6. የስራ ጠረጴዛችንን ጽዱ እና አቀማማጡን የተስተካከለ ማድረግ

ቤታችን ንጹህ ሲሆን ደስ የሚለንን ያህል ቢሮ ውስጥም ጠረጴዛችን ንጹህና ማራኪ አቀማመጡም የተስተካከለ ሲሆን በስራ ላይ የሚያጋጥምን ጭንቀት እንደሚቀንስ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የስራ መደራረብ ሲያጋጥም በአግባቡ ለመምራትም ያመቻል፡፡

7. ለ10 ደቂቃዎች መመሰጥ

በስራ ሰዓት ካለን ጊዜ ውጥ 10 ደቂቃ ያህል ከቢሮ ወጣ ብሎ ፀጥታ በነገሰበት ቦታ ተመስጦ አድርጎ ወደ ስራ መመለስ ጭንቀትን አስወግዶ ብሩህ መንፈስን ያላብሳል፡፡

በተመስጦው ጊዜም ዓይንን መጨፈን፣ ትኩረትን መሰብሰብ፣ አተነፋፈስን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

8. በረዥሙ አየር ወደ ውስጥ ማስገባትና ማስወጣት

አንድ ሰው በስራ ገበታው ላይ እያለ ለትከዜ ወይም ለጭንቀት የሚዳርግ ሀሳብ ወደ አዕምሮው ከመጣ ስራውን ለአፍታ አቁሞ አየር ወደ ሳንባ በጥልቁ ማስገባት ለመረጋጋት ቢሞክር የተሻለ መሆኑን የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የባዮኬሚስትሪ ፕሮፌሰሩ ማርክ ክራስኖው ይናገራሉ፡፡

አተነፋፈስን ማረጋጋት አዕምሮን ለማረጋጋት ወሳኝ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር ክራስኖው፡፡

9. ጭንቀት ሲፈጠር የሚሰማንን በሙሉ መጻፍ

አስጨናቂ ነገሮች ወደ አንጎላችን በሚመጡበት ጊዜ ያለውን ስሜት በሙሉ በወረቀት ወይም በማስታወሻችን ማስፈር ይገባል፡፡

ስለምናስበው ነገር በምንጽፍበት ጊዜ ሁሉም ነገር በየመስመሩ ይቀመጣል፤ ይህ ደግሞ ለአዕምሮ እረፍትን ያመጣል ነው የሚሉት የስነ ልቦና ባለሙያዎቹ፡፡

10. በእግር ጉዞ ማድረግ

አንዳንድ ጊዜ ከቢሮ ወጣ ብሎ ለ10 ደቂቃ ያህል በእግር እንቅስቃሴ ማድረግ የመንፈስ መታደስን ለማምጣት ይረዳል፡፡

የእግር ጉዞ ማድረግ አዕምሮን በማረጋጋት በስራችን ላይ ውጤታማ እንድንሆን እንደሚያግዝም ተጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተገለፁት ተግባራት በአማራጭነት የሚተገበሩ ሲሆኑ ከ10 ደቂቃ ውስጥ ባነሰ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትን ለማስወገድ ቁልፍ መፍትሔ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement