NEWS: ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ አክሲዮን ማህበርና አንቦ ማዕድን ውሃ አክሲዮን ማህበር ህገ-ወጥ የውህደት ድርጊትና የውህደት ቅንብር ፈፅመዋል በሚል ለቀረበባቸው ክስ ዛሬ መልስ ሰተዋል፡፡

                                                                                      

(ንጋቱ ረጋሳ)

ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ አክሲዮን ማህበርና አንቦ ማዕድን ውሃ አክሲዮን ማህበር ህገ-ወጥ የውህደት ድርጊትና የውህደት ቅንብር ፈፅመዋል በሚል ለቀረበባቸው ክስ ዛሬ መልስ ሰተዋል፡፡

ሁለቱ አክሲዮን ማህበራት ህገ-ወጥ ውህደት በመፈፀም ተገቢ ያልሆነ ውድድር ፈጥረዋል በማለት የከሰሳቸው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡

ባለሥልጣኑ እንዳለው የአክሲዮን ማህበራቱ ኃላፊዎች ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ውህደት መፈፀማቸውን በቃል ተናግረዋል፡፡

በአከፋፋዮች ላይም የሁለታችንንም ምርቶች ነው መያዝ ያለባችሁ የሚል ግዴታ አስቀምጠዋል፡፡

አንዱ የሌላውን አርማና የንግድ ምልክት መጠቀሙንም ባለሥልጣኑ በክሱ ላይ አስፍሯል፡፡
ሁለቱ አክሲዮን ማህበራት በጋራ የሥራ አመራር አቅጣጫ ነድፈዋልም ብሏል፡፡

የአንዱን አክሲዮን ማህበር ሠራተኛ ወደ ሌላው የማዘዋወር ተግባር ፈፅመዋል ሲልም ባለሥልጣኑ በክሱ ላይ አስፍሯል፡፡

እነዚህ ተግባሮች በሁለቱ አክሲዮን ማህበራት መካከል ውህደት ወይም መቀላቀል መፈጠሩን የሚያረጋግጡ ናቸው ብሏል፡፡

ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግና አንቦ ማዕድን ውሃ አክሲዮን ማህበራት በቃል ተዋህደናል ብላችኋል ተብሎ የተነገረው ስህተት ነው፣ ብንል እንኳ ውህደት የሚፈፀመው ብዙ ሂደት አልፎ በሰነድ ነው እንጂ በቃል አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

አከፋፋዮች የሁለታችንንም ምርቶች እንዲይዙ ግዴታ አስቀምጣችኋል መባላችንም ስህተት ነው ሲሉም መልሰዋል፡፡

አንዱ የሌላውን አርማ ተጠቅሟል በሚል የቀረበው ክስም ትክክል እንዳልሆነ በመቃወሚያቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

በድርጅቶች መካከል ሰራተኛ መዋዋስ በኢትዮጵያ የተለመደ አሰራር መሆኑን በመጥቀስ ይህንን የሚከለክል ህግ የለም ሲሉም ተከራክረዋል፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ አክሲዮን ማህበራት መካከል የተፈጠረ ውህደት የለም፤ ይህንን የሚያሣይ ማስረጃም በከሣሾቹ በኩል አልቀረበም ብለዋል፡፡

ጉዳዩን እያየ ያለው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የዳኝነት ችሎትን ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 17 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡

 

Advertisement