ታሪክን የኋሊት – የኮንኮርድ አውሮፕላን ነገር::

                                            

(የኔነህ ከበደ)

ኮንኮርድ የተሠኘው ከድምፅ የፈጠነ ሱፐር ሶኒክ የመንገደኞች አውሮፕላን በ27 ዓመት የአገልግሎት ዘመኑ አንዳችም የደህንነት እንከን አልታየበትም ነበር፡፡

የዛሬ 17 ዓመት የዛሬዋ እለት ለኮንኮርድ መራራ እለት ሆነች፡፡

በእለቱ ኤር ፍራንስ ኮንኮርድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር 4590 ከፓሪስ በኢኳደር በኩል ወደ ኒውዮርክ ለመብረረር አኮብኩቦ ተነሳ፡፡

አየር ላይ ብዙም አልቆየ፡፡

የሚትጐለጐል የእሳት ኳስ መትፋት ጀመረ፡፡

ከአንድ ሆቴል አቅራቢያም ተከሰከሰ፡፡

በውጤቱም ከ100 መንገደኞችና ከዘጠኙ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ለወሬ ነጋሪ የተረፈ አልነበረም፡፡ በአደጋው በመሬት ላይ የነበሩ ሌሎች አራት ሰዎችም ሞቱ፡፡

ኮንኮርድ የብሪታንያና የፈረንሳይ ትብብር የታየበት፤ የሁለቱ ሀገሮች የአውሮፕላን እነፃ ኢንጂነሮች የተጠበቡበት በዘመኑ ዘመን አፈራሽ ተብሎ የተደነቀ የተጨበጨበለት ነበር፡፡

ይህ ከድምፅ የፈጠነ ከተፎ አውሮፕላን ኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና አትራፊነቱ ተመሠከረለት፡፡ 
በመንገደኞች አውሮፕላን ታሪክ በፍጥነቱ አቻም፤ ወደርም አጣ፡፡

ከፈጣንነቱ የተነሳ የአትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ ለማዶውን በረራ ከየትኛውም ሌላ ስሪት አውሮፕላን ባነሰ ጊዜ ማቋረጥ መቻሉ ትርፋማነቱን አሳደገው፡፡

ኤር ፍራንስንም ሆነ ብሪቲሽ ኤርዌይስን አኮራቸው፡፡ ካዝናቸውም በትርፍ ሞላው፡፡

በሰዓት ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በመክነፍ አትላንቲከ ውቅያኖስን በ3 ሰዓት ተኩል ጊዜ ፉት ብሎ ጉዞው የሚጠይቀውን የጊዜ ርዝመት ጐምዶ ያስቀረ ነበር፡፡

ይሄ ዝና፤ ይሄ አድናቆት ሳይደበዝዝ የዛሬ 17 ዓመቱ አደጋ ስጋትን ፈጠረ፡፡ እንደሚባለው ኮንኮርድ ከመነሳቱ ደቂቃዎች በፊት የበረረ ዲ.ሲ 10 አውሮፕላን በማከብከቢያ ሜዳው ቁራጭ የብረት ዘንግ ጥሎ ይነሳል፡፡

ኮንኮርድ ሲያኮበኩብ ይሄን የብረት ዘንግ መትቶ ይንሸራተታል፡፡ በጐማ የተመታው የብረት ዘንግ የነዳጅ ታንከሩን ይመታል፡፡

ይሄ አውሮፕላኑ በእሳት እንዲያያዝ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡

ከአደጋው በኋላ የኮንኮርድን ጐማ፣ የነዳጅ መያዣ ታንኮር የኤሌክትሪኩን ሁኔታ ደህንነት ለማሳደግ ለ3 ዓመታት ጥረት ሲደረግ ቆየ፡፡

ከፓሪሱ አደጋ አንድ ዓመት በኋላ ኮንኮርድ ዳግም ወደ በረራው ተመለሰ፡፡

ይሁንና ከ14 ዓመታት በፊት ኤር ፍራንስም ሆነ ብሪቲሽ ኤር ዌይስ ኮንኮርድ በቃ፤ ይብቃው አሉ፡፡

የ27 ዓመታት የአየር ላይ ንጉሱ ኮንኮርድ ጡረታ ወጣ፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

Advertisement