NEWS: በአፍጋኒስታን ካቡል በተፈፀመ የሽብር ጥቃት የ24 ሰዎች ህይወት አለፈ::

                                               

በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል በአጥፍቶ ጠፊ በተፈፀመ የሽብር ጥቃት የ24 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።

የአፍጋኒስታን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት፥ የሽብር ጥቃቱ በተሽከርካሪ ላይ በተጠመደ ቦምብ ነው የተፈፀመው።

በጥቃቱም ህይወታቸውን ካጡ 24 ሰዎች በተጨማሪ 42 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።

የካቡል ከተማ ባለስልጣናት በበኩላቸው፥ የሽብር ጥቃቱ ፈፃሚ በተሽከርካሪው ላይ ያጠመደውን ቦምብ የሺአ እስልምና ተከታዮች በሚበዙበት አካባቢ ላይ ማፈንዳቱን አስታውቀዋል። 

የጥቃቱ ኢላማ እነማን እንደሆኑ በግልፅ ያልታወቀ ሲሆን፥ ለጥቃቱም አስካሁን ሀላፊነት የወሰደ አካል የለም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ሲፈፀሙ የነበሩ የሽብር ጥቃቶች በብዛት በታሊባን የታጣቂዎች ቡድን እና በአሸባሪው አይ ኤስ እንደነበሩ ይታወቃል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍጋኒስታኗ ካቡል በርካታ የሽበር ጥቃቶች እየተፈፀሙባት ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ በቅርቡ የተፈፀመው እና ከ150 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የሽብር ጥቃት አንዱ ነው። 

እንደ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት፥ በአውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2017 ግማሽ ዓመት ብቻ 1 ሺህ 662 አፍጋኒስታናውያን በሽብር ጥቃት ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

በሽብር ጥቃቱ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች ውስጥ ደግሞ 20 በመቶ ያክሉ የካቡል ነዋሪዎች መሆናቸውንም ሪፖርቱ ያመለክታል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

 

 

Advertisement