ጭቅጭቅን ማስቆሚያ 4 የፍቅር ዘዴዎች | Four Argument Avoiding Tips

                                                

ፍቅረኛሞች ናችሁ እንበል፡፡ ግንኙነታችሁ ይህን የሚመስል ከሆነ አልፎ አልፎ መጨቃጨቃችሁ ወይም መጣላታችሁ አይቀርም፡፡ ይሁን እንጂ በፍቅረኛችን መበሳጨቱም ሆነ መናደዱ፣ ጭቅጭቁን እንዴት ማስተናግድ እንዳለብን እስካወቅን ድረስ፣ የፍቅር ግንኙነቱን ሊንደው አይገባም፡፡

1. ሁለት አይነት ችግሮች መኖራቸውን መገንዘብ
ከፍቅረኛችን ጋር ባለን ግንኙነት ስንበሳጭ ወይም ስንናደድ አብዛኛውን ጊዜ ሁለት የተለያዩ ችግሮች ይኖራሉ፤ እነኚህም ችግሮች ስሜታችንና ችግሩ ራሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ ፍቅረኛሽ የተበላባቸውን ሳህኖች ባለማጠቡ ተበሳጭተሻል እንበል፡፡ ይህን ጊዜ መፍታት ያለብሽ ሁለት ችግሮች አሉ፤ ሳህኖቹ መታጠብ ያለባቸው ሲሆን፣ ፍቅረኛሽ ይህን ባለማድረጉ መበሳጨትሽንም ማቆም አለብሽ፡፡
በአብዛኞቹ ሌሎች የህይወት ዘርፎች ለችግሮችን ቅድም ተከተል በመስጠት በተናጠል ልንፈታቸው ይገባል፡፡ የፍቅር ግንኙነታችንን በተመለከተ የሚፈጠሩ ግጭቶችንም ቢሆን በተመሳሳይ መልኩ ማስተናግዱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ‹‹ስለ… ብለህ አንዴ እንኳን ሳህኖቹን ብታጥባቸው ምን አለበት?›› የሚለውን የመሰለ ጥያቄ ከመሰንዘራችን በፊት ውጤታማ ውይይቶችን አስቸጋሪ የማናደርግ ምክንያታዊ ሰው መሆናችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡
በፍቅረኛችን ምግባር ወይም አድራጎት ተበሳጭተን ቅሬታችንን ከመግለፅ መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ፣ በመሳጨትና ንዴታችንን መግለፅ የተለመደ ነው፤ ምንም ነገር ሳናደርግ ያለማቋረጥ በችግሮቻችን ዙሪያ መቆዘሙ ግን ይበልጥ እንድንናደድ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ስሜታችን መፍትሄ የሚያስፈልገው ነገር እንደሆነና የጭቅጭቁ መንስኤ ከሆነው ጉዳይ የተለየ እንዲሆን መቀበሉ ወደ መፍትሄው የሚያቀርበን እርምጃ ነው፡፡

2. በቀዳሚነት ስሜታችንን ማስተናገድ
ንዴት፣ መቆጣጠር በተመለከተ ማንኛችንም ብንሆን የምንረጋጋበት የየራሳችን መንገድ አለን፡፡ ከፍቅረኛችን ጋር ለመጣላት ከደረሰን፣ ሁኔታው በውስጣችን የፈጠረውን ውጥረት ለማስተናግድ ፋታ ልናገኝ ይገባል፤ ሌላኛውም ወገን እንዲሁ በተመሳሳይ ሂደት በኩል ማለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ውጥረት ለብቻ ማስተናገዱ የተሻለ ነው፤ ይሁንና፤ በአንዳንድ ስሜትን የሚነኩ ሁኔታዎች ባለንበት ቦታ ሆነን ለረዥም ጊዜ መተንፈሱ እገዛ ሊኖረው ይችላል፡፡ ለማንኛውም በውስጣችን የተፈጠረውን ውጥረቱን የሚያቃልሉ ነገሮችን እናድርግ፤ የእግር ጉዞ ማድረግ፤ ሞቅ ያለ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ አሊያም ንዴታችንን በወረቀት ላይ አስፍረን ቀድደን መጣል እንችላለን፡፡
ይህ አካሄድ የተሻለ ውጤት የሚያስገኘው ፍቅረኛችን ቀደም ብለው ውጥረትን በምን አይነት መንገድ እንደምናስተናግድ ካወቁ ነው፡፡ መቆናጠር፣ እንዲሁም ማጉረምረም የሌላኛውን ሰውን ስሜት በቀላሉ የሚጎዱ ናቸው፡፡ ራሳችንን በጭቅጭቅ መሃል ውስጥ ከማግኘታችን በፊት ፍቅረኛችን ንዴትን በምን መልኩ እንደሚያስተናግዱ ማወቅና ምን እንደምንፈልግ እንደሚያውቁ ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ እንዲያውም፣ ‹‹የፈለግሽውን…›› ከማለት ይልቅ፣ ‹‹የእግር ጉዞ ማድረግ አለብኝ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እናወራለን›› ማለቱ ይበልጥ ጠቃሚ ነው፡፡

ከሁሉም የበለጠ አንዴ ከተረጋጋን ወደነበርንበት ቦታ መመለሳችን ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ ጭቅጭቅ ሲፈጠር ሁለት የተለያዩ ችግሮችን እያስተናገድን ነው፡፡ መረጋጋቱ አንዱን ችግር ሲፈታ ሁሉም ነገር ከበፊቱ የተሻለ ነው የሚለው ስሜትም በቀላሉ ይከተላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ቀለል ቢሉልንም፣ ከፍቅረኛችን ጋር ያለን ችግር ችክ ያለ ከሆነ ስለተረጋጋን ብቻ ይጠፋል ማለት አይደለም፡፡

3. ከሄድንበት ስንመለስ ሁኔታውን ማስተናገድ
አንዴ ከተረጋጋን ችግራችንን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መመልከት ልንጀምር እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ ረገድ ሁኔታውን የምናስተናግድበት ጥሩና የተሻለ ስሜት ላይ እንገኛለን፡፡ ፍቅረኛሽ አድካሚ ቀን ካሳለፈ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የበላበትን ሳህን ባለማጠቡ መጨቃጨቁ ጥቅም የለውም፡፡ በሌላ በኩል፣ ምሽቱን አብራችሁ ሳታሳልፉ አስራ ሁለት ቀናት ካለፉ መነጋገሩ አይከፋም፡፡

ከፍቅረኛሽ ጋር ለመነጋገር ከሄድሽበት ቦታ ስትመለሺ ሁኔታዎችን በትብብር መንፈስ ተመልከቻቸው፡፡ በመካከላችሁ የተፈጠረውን ችግር አንዳችሁ ከሌላኛው አንፃር ከተመለከታችሁት፣ ደስተኛ የፍቅር ግንኙነት መመስረቱን ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ከስሜታችን ጋር የተያያዘ ብቻ ይሆናል፡፡ ‹‹እራት ስንበላ ሞባይል ስልክህን መነካካትህ ችላ የተባልኩ ሆኖ እንዲሰማኝ ያደርገኛል›› ማለቱ በቤት ውስጥ ስራ ሳቢያ የሚፈጠሩ ጭቅጭቆችን ያህል ምክንያታዊ ችግር ነው፡፡ ዋናው ነገር ጉዳዩን ሁለታችሁም ልትፈቱት የምትችሉት ነገር እንደሆነ አድርጎ መግለፁ ነው፡፡
በችግሩ ዙሪያ የሚደረገው ውይይት እንዳበቃ እርምጃ መውሰዳችሁን ማረጋገጥ ይኖርባችኋል፡፡ የመግባባት ችሎታችሁ ጠቃሚ ከመሆኑም ሌላ፣ ከፍቅረኛችን ጋር የበለጠ መተሳሰርን ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ሁኔታዎች እንደ በፊቱ ሆነው ካልተለወጡ ግን ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያንኑ ንግግር መድገም ሊኖርባችሁ ነው፡፡ ሁለታችሁም መለወጥ ያለበት ነገር ምን እንደሆነ ከስምምነት ላይ ከደረሳችሁ፣ ጥሩ ልምዶችን ለማዳበር የምትጠቀሙባቸውን ስልቶች ተግባራዊ አድርጉ፡፡ ፍቅረኛሽ እንዲደመጥ የሚፈልገውን በተመለከተ ራስሽን ከማስታወስ አትቦዝኚ፡፡ በማስታወስ ችሎታሽ ላይ ብቻ አትተማመኚ፡፡

4. መታረቅ
ተናድደን ነበር፡፡ በቀጣይነት ከተረጋጋን በኋላ በችግሩ ዙሪያ ከተወያየን በኋላ መለወጥ ስላለበት ነገር እቅድ እናወጣለን፡፡ ይህን ጊዜ ነገሮች ጥሩ መስለው ይታዩናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ጥሩም ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ሂደቱን እዚህ ላይ አቁመን እጆቻችንን አጣጥፈን ብንቀመጥ እርስ በርስ መጯጯኹ ምን እንዲፈየድልን በቅጡ ለመረዳት እንቸገር ይሆናል፡፡ ስለዚህም፣ ሂደቱ የዘወትር ልማድ መሆኑን ለማረጋገጥ ራሳችንን እንሸልም፡፡
መተቃቀፍ፣ ፊልም ማየት፣ አሊያም ወሲብ መፈፀም ጭቅጭቁን በጥሩ መንፈስ ከፍፃሜ እንዲደርስ የሚያግዙ አዎንታዊ ዘዴዎች ናቸው፤ ይሁንና፤ ችግሩ መፍትሄ ሳያገኝ ወሲብ መፈፀም የፍቅር ግንኙነቱን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ የፍቅረኛችን ከአጠገባችን መኖር ያስደስተናል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በጉዳዩ ዙሪያ ጤናማ ውይይት ካካሄዱ፣ አብረው የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል፡፡

ምንጭ:- ዘ ሳኮሎጂስት

Advertisement