ማህበራዊ ሚዲያዎች ወጣቶችን ለጭንቀትና ፍርሃት እንደሚዳርጉ ተመራማሪዎች ገለጹ::

                                              

የማህበራዊ ትስስር ገጾች በበርካቶች ዘንድ ተመራጭና የመገናኛ ዘዴዎች ከሆኑ ውለው አድረዋል።

የስነ ልቦና እና የህክምና ባለሙያዎች ደግሞ እነዚህ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ካላቸው ጠቀሜታ ባሻገር የጎንዮሽ ጉዳት እንደሚያስከትሉም ይገልጻሉ።

ከዚህ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥናትና ምርምሮች ደግሞ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ብዙ ጊዜ ማሳለፉ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ይገልጻሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በወጣቶች ላይ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በእንግሊዝ የተደረገ ጥናት ውጤት ይፋ ሆኗል።

ጥናቱ እድሜያቸ ከ12 እስከ 20 አመት የሚደርሱ ከ10 ሺህ በላይ ታዳጊና ወጣቶችን ያካተተ ነው።

በጥናቱ የወጣቶቹ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ተፈትሿል።

በዚህም ወደ 70 በመቶ የሚሆኑት በማህበራዊ ሚዲያ ሱስ የተጠመዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

17 በመቶዎቹ ደግሞ ለማህበራዊ ሚዲያ ቸልተኞች እንደሆኑና ይህን እንደማያጠቀሙ ገልጸዋል።

ማህበራዊ ሚዲያን የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት፣ ከሰዎች ጋር ለመገናኘትና ለመወያየት እንዲሁም ስሜታቸውን ለመግለጽና ሁነቶችን ለመከታተል እንደሚጠቀሙበትም ይገልጻሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በማህበራዊ ትስስር ገጾች ስለተለያዩ ጉዳዮች እንደሚወያዩም ነው የገለጹት።

ከተጠቃሚዎች መካከልም 47 በመቶ ያክሉ በማህበራዊ ሚዲያ ውይይት ወቅት አላስፈላጊ ነገሮችን እንደማያነሱና እንደማይወያዩ አስረድተዋል።

ከዚያ ይልቅ መልካምና በጎ ነገሮችን እንደሚያነሱም ይጠቅሳሉ።

በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል 40 በመቶ ያክሉ በማህበራዊ ገጻቸው ግድግዳ ላይ የለጠፉትን ነገር ሌሎች ሰዎች ካልወደዱትና ካልተጋሯቸው መጥፎ ስሜት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

35 በመቶዎች ደግሞ የራስ መተማመናቸው በማህበራዊ ትሰስር ገጾች ባላቸው ተከታታይ ብዛት የተወሰነ ነው ብለዋል።

ባለሙያዎች ግን ይህን መሰሉ አካሄድ ወጣቶችን ከእውነታው የወጣ ስብዕና ባለቤት ያላብሳል ነው የሚሉት።

ይህ የወጣቶቹ የበዛ የማህበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት ደግሞ፥ ማንነታቸው፣ ፀባያቸው እና ስብዕናቸው ላይ የራሱን ተፅዕኖ ያሳርፋልም ነው ያሉት ባለሙያዎቹ።

በዚህ መሰሉ የማህበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት የተጋለጡት ደግሞ ለከፍተኛ ጭንቀትና ፍርሃት የተጋለጡ እንደሆኑም አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ይህ የማህበራዊ ትስስር ሚዲያ ሱሰኝነት ወጣቶችን ወዳልተፈለገ ጭንቀትና ፍርሃት ይመራቸዋል ብለዋል በጥናታቸው።

ምንጭ:- FBC

Advertisement