በ2009 ዓ.ም.92 ሺ ቤቶችን አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ያታቀደ ቢሆንም የደረሱት ግን 39 ሺ 249 ብቻ ናቸው።

በብድር የሚገኘው ገንዘብ ዘግይቶ መለቀቁ ቤቶችን በተያዘው ጊዜ ገደብ ገንብቶ እንዳያጠናቅቅ ምክንያት እንደሆነው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ፤ ባንኩ ብድር  ያልሰጠው ተቋሙ የፋይናንስ አጠቃቀም ሪፖርት በወቅቱ ባለማድረሱ መሆኑን ገልጿል።

የፕሮጀክተ ጽህፈት ቤቱ በ2009 ዓ.ም. በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ 91 ሺ 900 ቤቶችን አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ያቀደ ቢሆንም የደረሱት ግን 39 ሺ 249 ብቻ ናቸው።

በኮዬ ፈጬ፣ የካ አባዶ፣ እና ቦሌ ቡልቡላ የሚገኙ 52 ሺ 651 ቤቶችን ለማጠናቀቅ ቢታቀድም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚገኘው የቦንድ ብድር በመዘግየቱ ምክንያት ማሳካት እንዳልተቻለ የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አረጎት አለሙ ገልፀዋል።

የታቀደውን ያህል ቤቶች አጠናቆ ለማስረከብ የ16 ቢሊዮን ብር ብድር የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ ባንኩ ያበደረው ግን ስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ከተገኘው ብድር ውስጥም ስራ ላይ የዋለው አምስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ነው።

ብድሩ የተገኘው የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ስድስት ወር ሲቀረው መሆኑ ደግሞ የተገኘውን ብድር ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም እንዳላስቻለ ነው አቶ አረጎት የተናገሩት።

ብድሩ በመዘግየቱ ምክንያት “የተበተኑ ስራ ተቋራጮችና ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንደገና አሰባስቦ ስራ ማስጀመሩ  አስቸጋሪ ነበር” ብለዋል።

በጽህፈት ቤቱ ያሉ የአሰራር ችግሮችም ገንዘቡን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ እንዳደረጋቸው ነው አቶ አረጎት የተናገሩት።

እነዚህ ቤቶች አሁን ላይ አፈፃፀማቸው 70 በመቶ አካባቢ የደረሰ  ሲሆን፤ 26 ሺ 480ዎቹን በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ መታሰቡን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙዩኒኬሽን ክፍል ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ በልሁ ታከለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ባንኩ ብድር የሚሰጠው ተቋሙ የፋይናንስ አጠቃቀም ሪፖርት ሲያቀርብ ነው።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የፋይናንስ አጠቃቀም ሪፖርት ሐምሌ 2008 ዓ.ም ላይ እንዲልክ መጠየቁን አውስተው፤ ለንግድ ባንኩ ሪፖርቱ የደረሰው በታህሳስ 2009 ዓ.ም በመሆኑ በጥር ብድሩን ለጽህፈት ቤቱ እንደተሰጠ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የጽህፈት ቤቱን አደረጃጀት ለመቀየር ረቂቅ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

 

ምንጭ፡ኢዜአ

 

 

Advertisement