የኤርትራ መንግስት በአፍሪካ ህብረት የተላከውን የልዑካን ቡድን አልቀበልም አለ

በጀቡቲና ኤርትራ አጨቃጫቂ ድንበር ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው ውጥረት መፍትሄ ለማፈላለግ የአፍሪካ ህብረት ልዑካን ቡድን አዋቅሮ ወደ ኤርትራ ቢልክም ኤርትራ ለልዑካን ቡድኑን ሳትቀበል ቀርታለች፡፡ ህብረቱ ልዑካን ቡድን አዋቅሮ መላኩን አስመልክቶ ቢቢሲ እንደዚሁም ዋሽንግተን ፖስትና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኋን በዘገባዎቻቸው አመልክተዋል፡፡

ሁንና የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በሰጡን ማብራሪያ የኤርትራ መንግስት ለዑካን ቡድኑን ያልተቀበለ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ እንደ አቶ መለሰ ገለፃ የሁለቱ ሀገራት ፖለቲካዊ ወጥረት የተነሳው የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሁኔታ ሲመለከት በነበረው ኢጋድ በኩል ሲሆን ጉዳዩንም የአፍሪካ ህብረት ከተመለከተው በኋላ ነበር ልዑካን ቡድኑ እንዲዋቀር የተደረገው፡፡

በጂቡቲና ኤርትራ ደንበር አካባቢ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት የራስ ዱሜራ ግዛት በሰላም አስከባሪነት ሰፍሮ የነበረው የኳታር ጦር አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የኤርትራ ጦር አካባቢውን መቆጣጠሩን የሚያሳዩ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ በኳታርና በአካባቢው ዓረብ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጥ ተከትሎ ኤርትራ ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል፡፡ጂቡቲ በአንፃሩ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ግንኙነት በተወሰነ ደረጃ እንዲገደብ ማድረጓን ተከትሎ ኳታር ጦሯን ከሁለቱ ሀገራት አወዛጋቢ ክልል የማስውጣት እርምጃን ወስዳለች፡፡

የህብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ ሁኔታዎችን ከሚያባብስ ተግባር እንዲቆጠቡ ጥሪ ማስተላለፋቸው ታውቋል፡፡

ቢቢሲ በዘገባው እንዳሰራጨው ከሆነ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ወደ ኤርትራ የላከው ልዑካን ቡድን የእውነት አፈላላጊ ቡድን (Fact finding mission) መሆኑን በመግለፅ ይህንንም የአፍሪካ ህብረት አቋም ኢትዮጵያ ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤትም ድጋፉን እንዲሰጥ ያሳሰበች መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል፡፡ ዘገባው ኢትዮጵያና ጂቡቲ የጋራ መከላከያ ስምምነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ጠቆም አድርጓል፡፡

ምንጭ፡-ሰንደቅ

 

Advertisement