የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የህብረት ስራ ቤት ግንባታ ተግባራዊ ይደረጋል

በአዲስ አበባ ያለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለማቃለል ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የህብረት ስራ ቤት ግንባታ ተግባራዊ እንደሚደረግ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ በተዘረጉ የጋራ መኖሪያ ቤት መርሃ ግብሮች በርካቶችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ ተችሏል።

ይሁን እንጅ መኖሪያ ቤቱን ለማግኘት ተመዝግበው ከሚጠባበቁት አንፃር የጋራ መኖሪያ ቤቱ አቅርቦት እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ነው።

በርካቶች በየዓመቱ በ3 ነጥብ 5 በመቶ እያደገ ከሚመጣው የመዲናዋ ነዋሪ ቁጥር አንጻርም የመኖሪያ ቤቱን አቅርቦት ለማሳደግ ሌላ አማራጭ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

የፋይናንስ አቅርቦት እጥረትና የግንባታ ብቃትና የፕሮጀክት አስተዳደር አቅም ማነስ፥ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ግንባታቸው ተጠናቆ ለተመዝጋቢዎቹ በጊዜ እንዳይተላፉ ማድረጉ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

የመዲናዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ሌሎች አማራጮች ተግባራዊ ለማድረግ ከጫፍ ደርሷል ነው የሚሉት።

የመንግስት ኪራይ ቤቶችን በከተማው ማስፋትና በህብረት ስራ ማህበራት ቤቶች እንዲገነቡ ማድረግ በአማራጭ የቤት አቅርቦትነት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

የከተማው አስተዳደር ይህን አማራጭ ተግባራዊ ሲያደርግ በከተማው በ2006 ዓመተ ምህረት በመኖሪያ ቤት የህብረት ስራ ማህበር የተደራጁ 110 ማህበራት ቦታ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።

እነዚህ በ110 ማህበራት የተደራጁት 200 ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች በተሰጣቸው ቦታ አፓርታማ ገንብተው ወደ ማጠናቀቁ ደርሰዋል ያሉት ከንቲባው፥ አስተዳደሩ ከዚህ ልምድ በመውሰድ የህብረት ስራ ማህበራት የቤት አቅርቦት ለመኖሪያ ቤት አማራጭ እንዲሆን ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ዓመት ተግባራዊ መደረግ በሚጀምረው የመኖሪያ ቤት የህብረት ስራ ማህበር የቤት አቅርቦት አማራጭ በመጀመሪያው ዙር 20 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች ይሳተፋሉ ተብሏል።

ለዚህም የብድር አቅርቦት ስርዓትን ጨምሮ መመሪያ የማሻሻል ስራ መጠናቀቁን ከንቲባ ድሪባ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በመኖሪያ ቤት የህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ ቤት ፈላጊዎች ቤት የሚሰሩበት ቦታ ተነሺዎች ካሉ፥ ማህበራቱ ለተነሺዎች ቦታ በማዘጋጀት እንዲያሰፍሩ ግዴታ ነበረባቸው።

ከንቲባው አዲስ በተዘጋጀው መመሪያ በርካታ የተለወጡ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ዝርዝር የአፈፃፀም ጉዳዮች በመመሪያው ተካተዋል ብለዋል።

ይህን ዝርዝር አሁን ይፋ ለማድረግ በከተማው ካቢኔ መፅደቅ እንዳለበትም አንስተዋል።

 የህብረት ስራ ማህበራቱ ለመኖሪያ ለሚሰሩት ቤት የሚሆን መሬት በጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ሳይቶችና በመሃል ከተማ መዘጋጀቱንም ከንቲባው አስረድተዋል።

ለቡን ጨምሮ የተለያዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ሳይቶችና አሁን በልማት በተነሱ አካባቢዎች በቀዳሚነት ለመርሃ ግብሩ ተዘጋጅተዋል።

እያንዳንዱ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ምን ያህል ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ በአፓርታማው ሊኖረው ይችላል የሚለው ጉዳይም የከተማውን ካቢኔ ውሳኔ ይጠብቃል ነው የተባለው።

የመኖሪያ ቤት ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ የሚገኘውን መሬት የመሸከም አቅም ባገናዘበ መልኩም፥ የቤቶች የወለል ብዛት የተለያየ ይሆናል ብለዋል ከንቲባ ድሪባ።

ህንፃዎቹ የቦታና የወጪን ቁጠባ መሰረት አድርገው የሚገነቡ በመሆኑ በአማካይ ከ10 በላይ ወለል ይኖራቸዋል።

ምንጭ፡-FBC

 

Advertisement