በሳውዲ አረቢያ ከሚኖሩ ህገ-ወጥ ዜጎች መሀከል 120 ሺ ያህል ኢትዮጵያውያን ሀገር ቤት ለመመለስ የጉዞ ሰነድ ቢወስዱም ግማሾቹ እንኳ አልመጡም

በሳውዲ አረቢያ ከሚኖሩ ህገ-ወጥ ዜጎች መሀከል 120 ሺ ያህል ኢትዮጵያውያን ሀገር ቤት ለመመለስ የጉዞ ሰነድ ቢወስዱም ግማሾቹ እንኳ አልመጡም ተባለ፡፡

 

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዛሬ ለሸገር እንደተናገረው የሳውዲ መንግሥት ከሀገሬ ውጡ የሚለውን ትዕዛዝ ካስተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ሀገር ቤት ለመመለስ የተመዘገቡ ኢትዮጵያውያን እጅግ በጣም ትንሽ መሆናቸውን ነው፡፡

 

ከሳውዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን በዘላቂነት ለማቋቋም እንዲቻል የተለያዩ ተቋማት በገቡት ቃል መሠረት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት 5 ሚሊዮን ብር መስጠታቸው ተነግሯል፡፡

 

በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመዘናጋት ላይ ናቸው ያሉት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ባልደረባ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይዞ የሚመለሰው ሰው ቁጥር ትንሽ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

 

እስካሁን ለመጡት 55 ሺ ገደማ ሰዎች ምን ተደርጓል ስንል የጠየቅናቸው የጽ/ቤቱ ባልደረባ ለተመላሾቹ ጊዚያዊ መጠለያነት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መዘጋጀቱንና ወደየ ክልሎቻቸው ለሚመለሱ ሰዎች ትራንስፖርት ተዘጋጅቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡

 

የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ቀደም ሲል ከሰጠው የ90 ቀናት በተጨማሪ 1 ወር ጊዜ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ህገ-ወጥ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ450 ሺ እንደሚበልጥም ይነገራል፡፡

ምንጭ-ሸገር ኤፍ ኤም

 

Advertisement