በአዲስ አበባ 30 የግል የትምህርት ተቋማት የእውቅና ፍቃድ ተሰረዘ

እውቅናቸው ተሰርዞ የእውቅና ሰርተፊኬት እንዲመልሱ የተደረጉት 18 የቅድመ መደበኛ 12 ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ተቋማት ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅርተ አበራ፥ ተገቢውን መስፈርት ሳያሟሉ የተገኙ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

በዚህም ከቦሌ ክፍለ ከተማ 4፣ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 4፣ ከየካ 5፣ ከኮልፌ 3፣ ከቂርቆስና ከጉለሌ ደግሞ አንዳንድ ተቋማት ፍቃዳቸው ተሰርዟል።

በሌላ በኩል ለቀጣይ 2010 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 79 አዳዲስ የትምህርት ተቋማት ፍቃድ የጠየቁ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ኤጀንሲው ለ33ቱ የማስተማር ፍቃድ ሰጥቷል።

የ1ኛ ደረጃ ትምህርትን በተመለከተ ደግሞ ከ35ቱ ውስጥ 10 አዲስ ፍቃድ የተሰጣቸው ሲሆን፥ 12ቱ መስፈርቱን እንዲያሟሉ በሂደት ላይ ሲሆኑ 13ቱ ደግሞ ከደረጃ በታች በመሆናቸው ተከልክለዋል።

ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለማስተማር የጠየቁ ተቋማት ጉዳይ እየታየ ይገኛል ተብሏል።

ምንጭ:- FBC

 

Advertisement