የኩፍኝ በሽታ በአውሮፓ እየተስፋፋ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገለፀ-በጀርመን 950 ሰዎች ሲጠቁ አንድ ሞት ተመዝግቧል

በአውሮፓ ባለፉት 12 ወራት ብቻ በኩፍኝ በሽታ 35 ሰዎች መሞታቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጠቃታቸው የበሽታውን በአሳሳቢ ሁኔታ መስፋፋት እንደሚያሳይ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የኩፍኝን መስፋፋት ለማስቆም ክትባቶችን ተደራሽ ማድረግም ወሳኝ መሆኑን ድርጅቱ ጠቁሟል፡፡

የአውሮፓ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል በፈርንጆቹ 2017 የመጀመሪያ አምስት ወራት የኩፍኝ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን ገልጿል፡፡

በሽታው የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በ2016 ዓመት ከነበረው በ50 በመቶ ብልጫ እንዳለው ማዕከሉ ጠቁሟል፡፡

በጣሊያን ብቻ ከፈርንጆቹ 2016 ሰኔ ወር እስከ ሰኔ 2017 3 ሺህ 300 ሰዎች በኩፍኝ መጠቃታቸው ተነግሯል፡፡

በሀገሪቱ በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ የተሰራጨ ሲሆን ካሳለፍነው ጥር እስከ ሰኔ ወር 3 ሺህ 232 የበሽታው ተጠቂዎች መገኛታቸው ተነግሯል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ በሀገሪቱ በበሽታው የተጠቁት ሰዎች ቁጥር 478 ብቻ ነበር፡፡

ጣሊያን ይህን የበሽታውን ተስፋፊነት ለመቀነስም በሚቀጥለው መስከረም ወር በስራ ላይ የሚውልና 12 የበሽታ መከላከያ ክትባቶችን ትግበራ የሚያስፈፅም መመሪያ አውጥታለች፡፡

በዚህም መሰረት በማንኛውም የመንግስት ትምህርት ቤት የሚማር ተማሪ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት እንዲወስድ ይደረጋል፡፡

በመላ ሀገሪቱ በሚደረገው የክትባት ዘመቻ ላይ ልጆቻቸው ክትባቱን እንዳይወስዱ የሚከለክሉ ወላጆች ካሉም በመመሪያው መሰረጥ ይቀጣሉ፡፡

በአውሮፓ አህጉር እየተስፋፋ ባለው ኩፍኝ በሮማኒያ ባለፉት 12 ወራት 3 ሺህ 922 ሰዎች ሲጠቁ፥ 31 ሰዎችም ሞተዋል፡፡

ሆኖም ባሳለፍነው ሳምንት የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ዘንድሮ የተከሰተው የኩፍኝ በሽታ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጾ፥ በቂ የክትባት ክምችት መኖሩን ጠቅሷል፡፡

በጀርመን 950 ሰዎች ሲጠቁ አንድ ሞት ተመዝግቧል፤ በፖርቹጋልም እንዲሁ በሽታው መከሰቱን ነው የአውሮፓ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል የገለጸው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት 95 በመቶ የሀገራቱ ዜጎች የኩፍኝ መከላከያ ክትባት እንዲከተቡ መክሯል፡፡

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል በበኩሉ ወደ ጣሊያን፣ ሮማኒያ እና ጀርመን የሚጓዙ ዜጎቹ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ አስጠንቅቋል፡፡

 

በክትባት መከላከል በሚቻለው በዚህ በሽታ ሰዎች መሞት እንደሌለባቸው በዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ዳይሬክተር ዶክተር ዜውዣና ጃካብ ተናግረዋል፡፡

ኩፍኝ በቫይረስ ተህዋስያን የሚመጣ በሽታ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታ በትንፋሽ እና በንክኪ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል፡፡

በሽታው ምልክቶች መካከል ከፍተኛ ትኩሳት፣ ሳል፣ የንፍጥ መብዛት፣ የዓይን መቅላት እና በእንባ መሞላት ጥቂቶቹ ናቸው።

ከሶስት እስከ አምስት ባሉ ቀናት ውስጥ በሰውነት ላይ የሽፍታ ምልክቶች ይከሰታሉ፡፡

ኩፍኝ ለሳንባ ምች እና መሰል በሽታዎች የማጋለጥ እድልም አለው፡፡

ይህ በሽታ በዋናነት እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ የመከሰት እድሉ ከፍተኛ ሲሆን በክትባት መከላከል ይቻላል።

 

ምንጭ፡- ሲ ኤን ኤን

 

Advertisement