የመን በኮሌራ በሽታ እየታመሰች ነው-300ሺህ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል

በጦርነት በፈራረሰችው የመን ባለፉት 10 ሳምንታት 300 ሺህ ዜጎች በኮሌራ ወረርሽኝ መጠቃታቸውን የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ።

ወረርሽኙ እጅግ አሳሳቢ እና ከቁጥጥር ውጭ በሚባል ደረጃ ደርሷል ያለው ቀይ መስቀል፥ በየቀኑ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው እንደሚጠቁ ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ባለፉት 10 ሳምንታት ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰዎች ከኮሌራ በሽታ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል ብሏል።

በየመን ሁለት አመት ያለፈው የመንግስት ደጋፊዎች እና የሃውቲ አማፂያን ግጭት የሀገሪቱን የጤና፣ የውሃ እና ፍሳሽ ስርአት ከጥቅም ውጭ እያደረገው ነው።

የአለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ ሰኔ 24 የመን በአለማችን ከፍተኛው የኮሌራ ወረርሽኝ የተከሰተባት ሀገር ናት፤ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል ሲል መግለፁ አይዘነጋም።

 

ከሁለት ሳምንት በኋላም በበሽታው የተጠቁት ዜጎች ቁጥር በ100 ሺህ መጨመሩን ነው የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የመካከለኛው ምስራቅ ዳይሬክተር ሮቤርቶ ማርዲኒ የተናገሩት።

የአለም ጤና ድርጅት ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በሀገሪቱ 297 ሺህ 438 ሰዎች በኮሌራ የተጠቁ መሆኑን መመዝገቡን የገለፀ ሲሆን፥ የአሃዙን አስተማማኝነት ለማረጋገጥም ከየመን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር እያጣራ መሆኑ ተጠቁሟል።

የመን ከ23 ግዛቶቿ በኮሌራ ያልተጠቃው አንድ ግዟቷ ብቻ ነው።

ሳና፣ ሁዳይዳህ፣ ሃጃ እና አምራን የተሰኙት ግዛቶቿ ደግሞ ክፉኛ በወረርሽኙ የተጠቁ ግዛቶች ናቸው የተባለ ሲሆን፥ ከአጠቃላይ የኮሌራ ተጠቂዎች ግማሽ የሚሆኑት በእነዚህ ግዛቶች እንደሚገኙም ተገልጿል።

ምንጭ:- FBC

 

 

Advertisement