በጋምቤላ ከእርሻ ኢንቨስትመንት 79 ባለሃብቶች በራሳቸው ፈቃድ ሥራ አቆሙ

በጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥር በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶችን የልማት እንቅስቃሴ አፈፃፀም ለማጥናት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ስር የተቋቋመው አጥኚ ቡድን በ2008 ዓ.ም ባደረገው ጥናትና በጣም ዝቅተኛ አፈፃፀም አሳይተዋል የተባሉ 269 ባለሀብቶች የእርሻ ኢንቨስትመንት ውላቸው እንዲቋረጥ በተወሰደው እርምጃ ቅር በመሰኘታቸው ለፌዴራልና ለክልሉ መንግስታት የቅሬታ አቤቱታ ያቀረቡትን የቅሬታ አቤቱታን መነሻ በማድረግ በፌዴራልና በክልሉ መንግስታት የተቋቋመው የቅሬታ አጣሪ ቡድን ከ07/09/2009 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ በመግባት የአቤቱታ አቅራቢዎችን አቤቱታ ሲመረምር ቆይቷል።

ቡድኑ ዝርዝር መረጃዎችን ከመረመረ በኋላ 186 ባለሃብቶች ወደሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ፣ 4 ባለሃብቶች ሙሉ ለሙሉ ከኢንቨስትመንት እንዲሰረዙ የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል። 79 ባለሃብቶች የተሰጣቸውን ቅሬታ የማቅረብ እድል ሳይጠቀሙ በራሳቸው ፈቃድ ከእርሻ ኢንቨስትመነት መሰናበታውን ሪፖርቱ አይዞ አስቀምጧል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ማጣራት እንዲደረግባቸው አቅጣጫ ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል በመልካም አስተዳደር ችግሮችና ሌሎች ምክንያቶች 21፣ የእፎይታ ጊዜያቸውን ያልጨረሱ 88፣ በመስክ የእርሻ ልማታቸው የታዩና ወደ ልማት የገቡ 43፣ ከተሰጣቸው ጊዜ አኳያ የሚፈለገውን ያክል ያላለሙና በከፊል ወደ ሥራ የገቡ ከተሰጣቸው ይዞታ በከፊል የተቀነሰባቸው 3፣ ጨርሰው ወደ ልማት ያልገቡ 4፣ የክልሉ ተወላጅ የሆኑና ወደ ሥራ የገቡ 4፣ የቅሬታ አቤቱታ ያላቀረቡ 79 ባለሀብቶች በተመለከተ እና የውሳኔ ሃሳብ የያዘ ሰነድ ለባለድርሻ አካት በሙሉ አጥኝው ኮሚቴ ሪፖርቱን መበተኑን የሰንደቅ ምንጮች ገልጸዋል።

ሪፖርቱ ባስቀመጠው ዝርዝር እንደሚያሳየው፤ በጣም ዝቅተኛ አፈፃፀም አሳይተዋል በማለት የተፈረጁት የእርሻ ኢንቨስትመንት መሬታቸው እንዲታገድ ውሳኔ ከተላለፈባቸው 269 ባለሀብቶች መካከል 190 የቅሬታ አቤቱታ አቅራቢ ባለሀብቶች በአካል ቀርበው ለኮሚቴው ባስረዱት እና የቀረቡ ሕጋዊ ሰነዶችን በመፈተሽ በተቀመጡት አምስት መመዘኛዎች በየፈርጁ መለየቱን አስቀምጧል።

በዚህም መሰረት ከ190 ቅሬታ አቤቱታ አቅራቢ ባለሀብቶች መካከል 27 የባንክ ተበዳሪዎች በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት እንዲቀጥሉ ኮሚቴው የውሳኔ አስተያየት ሰጥቷል።

በ2005 ዓ.ምና ከዚያ በፊት የእርሻ ኢንቨስትመንት ቦታ ተረክበው ምንጣሮ በ2008 ዓ.ም በተደረገው ጥናት ባለመያዙና በአሁኑ አጣሪ ኮሚቴ እንዲያዝ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከ190 ቅሬታ አቅራቢ ባሀብቶች መካከል 50 ባለሀብቶች የሰጡትን ማብራሪያ መነሻ በማድረግ ወደ ልማት ስለመግባታቸው አፈፃፀማቸውን ኮሚቴው በመስክ መልከታ እንዲረጋገጥ በተወሰነው ውሳኔ መሠረት በመስክ ምልከታው ከ50 ባለሀብቶች መካከል፣ በትክክል ወደ ልማት የገቡ 43 ባለሀብቶች በተደረገው የመስክ ምልከታ ወደ ስራ የገቡ በመሆኑ በልማቱ እንዲቀጥሉ የውሳኔ ሀሳብ በኮሚቴው ቀርበዋል።

በአቅም ውስንነት በከፊል ወደ ለማት የገቡ 3 ባለሀብቶች የመነጠሩትን የእርሻ ኢንቨስትመንት ቦታ ተለክቶ እንዲሰጣቸውና ቀሪው ወደ መንግስት የመሬት ቋጥ ተመላሽ እንዲደረግ ኮሚቴው በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።

እስካሁን ወደ ልማት ያልገቡ 4 ባሀብቶች የተረከቡት የእርሻ ኢንቨስትመንት ሙሉ በሙሉ ወደ መንግስት የመሬት ቋት ተመላሽ እንዲደረግ ኮሚቴው በአብላጫ ድምፅ የውሳኔ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

በ2006 ዓ.ም የመሬት ኪራይ ውል ፈርመው የእፎይታ ጊዜያቸውን ያልጨረሱ ከ190 ጠቅላላ ቅሬታ አቅራቢ ባለሀብቶች መካከል 88 ሲሆኑ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት እንዲቀጥሉ ኮሚቴው የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

በመልካም አስተዳደር ችግሮችና በሌሎች የተለያዩ ሕጋዊ ምክንያቶች ልማቱን ወደፊት ለማስኬድ ተግዳሮት የሆነባቸው ባለሀብቶች ከ190 ቅሬታ አቅራቢዎች መካከል 21 ሲሆኑ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት እንዲቀጥሉ ኮሚቴው የውሳኔ አስተያየት ሰጥቷል።

የክልሉን ተወላጆች ለማበረታታትና ለመደገፍ በተሰጠው አቅጣጫ ከ190 ቅሬታ አቅራቢዎች መካከል 4 ባለሀብቶች ወደ ልማት የገቡና የክልሉ ተወላጆች ስለሆኑ ኮሚቴው በልማቱ እንዲቀጥሉ በማለት የውሳኔ አስተያየት ሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ በጣም ዝቅተኛ አፈፃፀም አሳዩ ከተባሉት 269 ባለሀብቶች በተቀመጠው የቅሬታ አግባብ ቅሬታቸውን በአካል በመቅረብ ያስረዱ 190 ባለሀብቶች ሲሆኑ 79 ባለሀብቶች ግን ቅሬታቸውን ባለማቅረባቸው ምክንያት ኮሚቴው ጉዳያቸውን ማየት አልቻለም ሲል ሪፖርቱ የውሳኔ ሃሳቡን አጠቃሏል።

 

ምንጭ፡ሰንደቅ ጋዜጣ

 

 

 

Advertisement