ከባድ ዝናብና የመሬት መደርመስ የ3 ሰዎችን ሕይወት አጠፋ

በምስራቅ ሸዋ ዞን ሁለት ወረዳዎች በመሬት መደርመስና ከባድ ዝናብ ባስከተለው አደጋ ሶስት ሰዎች መሞታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የህዝብ ግንኝነት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ  እንደገለፁት የመሬት መደርመሱ ያጋጠመው በቦራ ወረዳ ሲሆን ከባድ ዝናብ ጉዳት ያደረሰው ደግሞ በፈንታሌ ወረዳ ነው ።

 በቦራ ወረዳ በዳሎሳ መቲ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሰምቦ በተባለ መንደር ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ አሸዋ በማውጣት ላይ በነበሩ 5 ሰዎች ላይ መሬት ተደርምሶ ሁለቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ ሶስቱ ከጉዳቱ በህይወት ተርፈዋል ።

 በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አስከሬንም ለቤተሰቦቻቸው የተሰጠ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

 በተመሳሳይም በፈንታሌ ወረዳ ዳራ ዲማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ላይ ከጧቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ለተከታታይ 5 ሰዓታት በጣለው ከባድ ዝናብ አንድ ቤት በመፍረሱ በውስጡ የነበረች የ30 ዓመት ወጣት ህይወት አልፏል።

 አደጋው በተከሰተበት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን የወጣቷን ህይወት ለማዳን በአቦምሳ መካከለኛ ክሊኒክ የህክምና ድጋፍ  ቢደረግላትም ማትረፍ እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

 በተለይ በክረምት ወራት አሸዋ ለማውጣት የሚደረገው ጥረት ከዝናብ ጋር ተያይዞ መሬቱ በቀላሉ ሊደረመስ ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ አሳስበዋል።

ምንጭ፡ኢዜአ

 

Advertisement