አዋሽ ባንክ 1.4 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዘገበ-ከግል ባንኮች ቀዳሚነቱን አስቀጥሏል፡፡

አዋሽ ባንክ በዓመቱ ያስመዘገበው ያልተጣራ ትርፍ 1,444,038,000 ብር ሲደርስ፣ ባንኩ ባለፈው የሒሳብ ዓመት ካስመዘገበው የ1,004,639,000 ብር ያልተጣራ ትርፍ የዘንድሮ በ439,399,000 ብር ብልጫ ማሳየቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አዋሽ ባንክ በ2008 የሒሳብ ዓመት በዳሸን ባንክ ተይዞ የነበረውን መሪነት ተቀብሎ የነበረ ሲሆን፣ ባንኩ በዚህ ዓመትም መሪነቱን ማስቀጠል ችሏል፡፡

ባንኩ ለዚህ ስኬት ለመብቃቱ ዋነኛ ሚናውን የተጫወተው ባንኩ የቀረፀው ‹‹ራዕይ 2025›› የተባለው ስትራቴጂ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ማርኬቲንግ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ኃይሉ ናቸው፡፡

አቶ አንዱዓለም እንዳሉት፣ የተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ባንኩ ‹‹ራዕይ 2025›› መተግበር የጀመረበት ዓመት ነው፡፡ በዚሁም ዓመት ባንኩ ይኼን ዓይነት ስኬት ማምጣቱ ባንኩ እየከተለ ያለው ስትራቴጂ ትክክለኛና ውጤታማ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

አዋሽ ባንክ ኬፒኤምጂ በተባለው አማካሪ ኩባንያነት አማካይነት እየተገበረ የሚገኘው ‹‹ራዕይ 2025›› ለአሥር ዓመታት የሚዘልቅ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዓመት የትግበራ ሥራው ባንኩ ያስቀመጣቸውን ግቦች ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን አቶ አንዱዓለም ገልጸዋል፡፡

አዋሽ ባንክ በ2009 የሒሳብ ዓመት ማብቂያ የተከፈለ ካፒታሉ 2,645,330,081 ብር የደረሰ ሲሆን፣ ዓምና ካስመዘገበው የ2,242,721 ብር አኳያ ሲታይ የ402,608,257 ብር ብልጫ ማስመዝገብ እንደቻለ ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ በ2009 የሒሳብ ዓመት ከ22.6 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱን የገለጹት ምንጮች፣ ባንኩ በቀዳሚው የሒሳብ ዓመት ከሰጠው የ15.5 ቢሊዮን ብር ብድር አንፃር ሲታይ የ7.1 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ሒሳቡ ዓምና ከነበረው 24.2 ቢሊዮን ብር በ8.5 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት 32.7 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑም ታውቋል፡፡

ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለይ ሁለት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ገጥመውት ነበር ተብሏል፡፡ የመጀመሪያው በኢንዱስትሪ ውስጥ ካለው ፉክክር የተነሳ፣ የተቀማጭ ሒሳቡና የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን በማሳደጉ ረገድ የገጠመው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ባንኩ እየተገበረ የሚገኘው የ‹‹ራዕይ 2025›› ያመጣው የመዋቅር ለውጥ ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ባንኩ ከከፍተኛ ኃላፊዎች ጀምሮ የተገበረው ለውጥ ከፍተኛ የሆነ የሥራና የኃላፊነት ሽግሽግ አስከትሎ ስለነበር፣ ለባንኩ ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑን አቶ አንዱዓለም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የአዋሽ ባንክ አጠቃላይ ሀብት 42.2 ቢሊዮን ብር በላይ መድረስ ችሏል፡፡ በዚህ ረገድ ሲታይም ባንኩ በ2009 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ሀብቱን ወደ 11.1 ቢሊዮን ብር በላይ ማሳደግ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ባንኩ 73 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት በአጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 313 ማድረስ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባንኩ 6,783 ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሠራ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባንኩ ‹‹ራዕይ 2025›› መተግበር የጀመረበት የመጀመሪያው ዓመት እንደመሆኑ መጠን፣ በቀጣይ ባንኩ ብዙ እንደሚጠበቅበት የማርኬቲንግና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ባንኩ ራዕዩን በመቀየርና የዓለማችን የመጀመሪያ ተመራጭ ባንክ በመሆን፣ በቀጣዮች አሥር ዓመታት ውስጥ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ አሥር ባንኮች ውስጥ አንዱ ይሆናል፤›› ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ 

 

ምንጭ፡ሪፖርተር

 

 

 

Advertisement