ሰበር ዜና: የመተሃራ ሰኳር ፋብሪካ በረዶ ቀላቅሎ በጣለ ዝናብ መክነያት ስራ አቆመ

በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ትናንት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ በረዶና ነፋስ ቀላቀሎ በጣለው ከባድ ዝናብ ጉዳት መድረሱን የስኳር ኮርፖሬሽን ገለፀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንዳስታወቀው፤ በአደጋው ምክንያት በዘጠኝ ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል።

ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አምስቱ በአዳማ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ በፋብሪካው ሆስፒታል በመረዳት ላይ ናቸው፡፡

በደረሰበት አደጋ ሳቢያ የፋብሪካው ግማሽ ጣሪያና ግርግዳ ፈርሷል፤ ሥራ ለማቆምም ተገዷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያጣራና ወደፊትም ፋብሪካው ሥራ የሚጀምርበትን ሁኔታ የሚያመቻች ኮሚቴ መቋቋሙን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

ፋብሪካው እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ 1 ሚሊዮን 50 ሺ ኩንታል ስኳር ለማምረት አቅዶ እየሰራ የነበረ ሲሆን፤ እስከ ትላንት ድረስ 823 ሺ 831 ኩንታል ስኳር አምርቷል፡፡

የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ኤች.ቪ.ኤ በተባለ የሆላንድ ኩባንያ ተገንብቶ በ1962 ዓ.ም. ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።
ምንጭ-ኢዜአ

Advertisement