ባንግላዲሻዊው አዛውንት በሁለት ቀን በትንሹ አንድ ዛፍ በመትከል ጫካ መስርተዋል::

                                         

አብዱል ሰመድ ሼክ በቅፅል ስም የዛፎች አባት የሚባሉት የ60 ዓመቱ ባንግላዲሻዊ በረዥም ጊዜ ውስጥ ለወደፊቱ የሚጠቅም ጥቂት ነገርን ማድረግ ዋጋው ከፍ ያለ መሆኑን በተግባራቸው እያሳዩ ነው፡፡

አዛውንቱ ከ12 ዓመታቸው ጀምሮ በየቀኑ ቢያንስ አንድ ዛፍ በመትከል ላለፉት 48 ዓመታት በርካታ ስራ አነስተኛ ጫካ መስርተዋል፡፡

እስካሁን የተከሏቸው ዛፎች ቁጥርም 17 ሺህ 500 ደርሷል፡፡

በማዕከላዊ ባንግዲሽ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ የተወለዱት አብዱል ሰመድ ሼክ ለስራ የሚንቀሳቀሱባት አንድ ባለ ሶስት እግር ብስክሌት አለቻው።

ዕለታዊ ገቢያቸው በሀገራቸው መገበያያ ገንዘብ 100 ታካ ወይም 1 ነጥብ 25 የአሜሪካ ዶላር ቢሆንም ለቤተሰባቸው የእለት ጉርስ ከሚያወጡት ባሻገር ቢያንስ አንድ የዛፍ ችግኝ ሳይገዙ ወደ ቤታቸው አይመለሱም፡፡

“የዓለም ጉዳይ የእኔም ሃላፊነት ነው” የሚሉት አዛውንቱ፥ በቀን ውስጥ ዛፍ ሳይተክሉ ቢቀሩ እንቅልፍ እንደማይወስዳቸው ይናገራሉ፡፡

ችግኞቹን ሌላ ሰው እንዳይቆርጥባቸው በመንግስት መሬት ላይ እንደሚተክሉ እና በየእለቱ ውሃ እንደሚያጠጡም ነው የሚገልፁት።

ሰዎች ዛፍ ሲቆርጡ ካዩ እንደሚያስቆሟቸው የተናገሩት አዛውንቱ አብዱልሰመድ፥ “ለሁሉም ፍጥረታት፣ ለእንስሳት በተለይም ለዛፎች የተለየ ፍቅር አለኝ” ብለዋል፡፡

እኝህ አባት የራሴ የሚሉት መሬት ስሌላቸው ከፋሪድፑር ከተማ ምክትል ኮሚሽነር ቢሮ፥ አጠገብ ባለ ስፍራ ላይ በሰሯት በሳር ቤት ውስጥ ነው ከሚስታቸው ጆርና እና ከአራት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት፡፡

አብዱል የቀን ገቢያቸው አናሳ ቢሆንም ሁልጊዜ ዛፍ ሳይተክሉ እንደማይውሉ የሚናገሩት ሚስታቸው ጆርና፥ አንዳንድ ጊዜ ይህን ስራ እንዲያቆሙ ስጠይቃቸው እርሳቸው ግን በየዕለቱ ችግኝ ከመትከል አይቦዝኑም ነው ያሉት፡፡

የ30 ዓመት ወንድ ልጃቸው ኩቱብ ኡዲን በበኩሉ፥ “አባቴ ለማህበረሰቡ የሚጠቅም ስራ እየሰራ በመሆኑ አንድም ቀን ስራውን እንዲያቆም ጠይቄው አላውቅም” ብሏል፡፡

አብዱል ሰመድ ሼክ በዚህ ዛፍ የመትከል የ48 ዓመት ጉዟቸው ላበረከቱት ትልቅ ስራ የባንግላዲሽ ዴይሊ ስታር ጋዜጣ ለቤተሰቦቻቸው ጥሩ ቤት እንዲሰሩ በሚል፥ የ100 ሺህ ታካ ወይም የ1 ሺህ 253 የአሜሪካ ዶላር ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡

አብዱል ሰመድ ከሽልማቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር ሁሉም ህብረተሰብ በቻለው ልክ ዛፍ በመትከል፥ ዓለማችንን ከጥፋት እንታደጋት የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ምንጭ፡- ዴይሊ ስታር

Advertisement