በሰንጋ ተራና ክራውን የተገነቡ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ቅዳሜ ይወጣል። በዕጣው ሁሉም ተመዝጋቢዎች ተሳታፊ እንደማይሆኑ ታውቋል

                                       

ላለፉት ሁለት ዓመታት በቅርቡ በዕጣ ይተላለፋሉ እየተባለ ሳይተላለፉ የቆዩ በሰንጋ ተራና ክራውን ሳይቶች የተገነቡ 972 ቤቶችና ከ320 በላይ የንግድ ቤቶች፣ በመጪው ቅዳሜ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በዕጣ እንዲተላለፉ ተወሰነ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ መገንባት የተጀመሩት ሁለቱ ሳይቶች በ18 ወራት ተጠናቀው በዕጣ ይተላለፋሉ የተባለ ቢሆንም፣ በተገባው ቃል መሠረት ተግባራዊ ሳይደረግ ላለፉት ሦስት ዓመታት ቆይተዋል፡፡

የቤቶቹን ግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ የሸፈነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆኑ፣ የቤቶቹ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆና ምንም ዓይነት ጉድለት ሳይገኝበት እንደሚረከብ በመግለጹና ኢንተርፕራይዙ በተለያዩ ጊዜያት ለማስረከብ ያደረገውን ሙከራ ባንኩ ባለመቀበሉ፣ ጊዜ መውሰዱን የባንኩ ኃላፊዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

አሁንም ቤቶቹን የተረከቡት ፍፁም የሆነ የግንባታ ሒደቶች ተጠናቀው ሳይሆን፣ አንዳንድ ጉድለቶችን በቀጣይ ለማስተካከል የሰነድ ፊርማ በመፈጸም መሆኑን ስማቸውን መግለጽ ካልፈለጉ የባንኩ ኃላፊዎች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

ቅዳሜ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በዕጣ የሚተላለፉት ቤቶች ቁጥር ከተመዝጋቢው አንፃር ሲታይ እጅግ በጣም ትንሽ በመሆናቸው፣ ሁሉም ተመዝጋቢዎች ተሳታፊ እንደማይሆኑ ታውቋል፡፡ በመሆኑም ኢንተርፕራይዙ በምዝገባ ወቅት ባወጣው የውስጥ መመርያ መሠረት፣ ቅድሚያ ሙሉ ክፍያ ለፈጸሙት ብቻ ዕጣ እንደሚወጣም ታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለ40/60 የጋራ ቤቶች ሙሉ ክፍያ የፈጸሙ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ወደ 17,000 በመድረሱ፣ ዕጣ የሚወጣላቸው በመጀመርያው የምዝገባ ወቅትና (ነሐሴ 2005 ዓ.ም. መጨረሻ) እንደ ቅደም ተከተላቸው በተመዘገቡበት ዕለትና ሰዓታት ጭምር ታይቶ የሚወዳደሩ መሆናቸውም፣ የባንኩና የኢንተርፕራይዙ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

ግንባታቸው ተጠናቆ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተላለፉት የሁለቱ ሳይቶች ቤቶች የውኃ፣ የመብራት፣ የመንገድ፣ የደረቅ ቆሻሻና የፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው መሆኑን ኢንተርፕራይዙ አስታውቋል፡፡ 

ምንጭ-ሪፖርተር

Advertisement