የጎንደር ዩንቨርሲቲ ቱሪስቶች በሞባይል የተሟላ መረጃ ማግኘት የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂ ፈጠረ።

 

ዩኒቨርሲቲው በሰሜንና ደቡብ ጎንደር የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን የሚያመላክት ካርታ ከማዘጋጀቱም በላይ አማርኛን ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ መተርጎም የሚያስችል ቴክኖሎጂ /የሞባይል መተግበሪያ አፕሊኬሽንም/ ፈጥሯል፡፡

የሞባይል መተግበሪያው በከተማው ስለሚገኙ አለምአቀፍ ቅርሶች አጭር መረጃን የሚሰጥ ሲሆን የመጓጓዣ አቅጣጫዎችንና የማረፊያ ቦታዎችንም ጭምር ለጎብኚዎች ጥቆማ መስጠት ይችላል፡፡

አማርኛን ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ የሚተረጉመው የሞባይል መተግበሪያ ደግሞ አስጎብኚዎች ከቱሪሰቶች ጋር በቀላሉ እንዲግባቡ፣ በሆቴሎች በምግብ ቤቶችና በግብይት ስፍራዎችም ቱሪስቶች ያለችግር አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ይረዳል፡፡

ለሁለቱ ዞኖች የሚያገለግለው የቱሪስት ካርታም ዋና ዋና ቅርሶች የሚገኙባቸውን ቦታዎች፣ ከዋና መንገድ ያላቸውን ርቀትና የክረምት ከበጋ የመንገድ አማራጮችን የሚያመላክት ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም ማኔጅመንትና በኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል በጋራ የተሰራው የሞባይል መተግበሪያ ፤ ኢንተርኔት አልባ ቦታዎች ላይ ጭምር መጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፍ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ለህብረሰሰቡ ጥቅም የሚውሉበትን መንገድ በማመቻቸት በኩል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መምሪያው የሞባይል መተግበሪያዎቹን በቱሪስት ማዕከላት በሆቴሎችና በተቋማት እንዲደርሱ በማድረግ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች በማስተዋወቅ  በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡

ጎንደር ከተማ በአለም ቅርስነት የተመዘገበውን የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትና የመዋኛ ስፍራን ጨምሮ የደብረብርሃን ስላሴና የቁስቋም ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መገኛ ነው፡፡

 ምንጭ-ኢዜአ

 

 

Advertisement