የአልኮል መጠጥን አብዝቶ በመጠጣት ምክንያት የሚጎዱ የሰውነት ክፍሎች – Organs Which Could Be Damaged by Consumption of Too Much Alcohol

                                                    

1) ልብ
ከልክ ያለፈ የአልኮል መጠጥ ማዘውተር የልብ ጡንቻዎችን በማዳከም የደም ፍሰት መዛባትን ያሰከትላል፡፡ በአልኮል መጠጥ ብዛት የሚከሰት የልብ ሕመም የትንፋሽ ማጠር፤ የተዛባ የልብ ምት፤ድካም፤የማያቋርጥ ሳልን ያስከትላል በተጨማሪም ለደም ግፊት እና ለድንገተኛ የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ይዳርጋል፡፡
2) አንጎል
የአልኮል መጠጥ በአንጎል ላይ መልዕክት መተላለፍን ያዘገያል፡፡አልኮል መጠጥን ማዘውተር የተለያዩ የአንጎል ክፍሎችን ስለሚጎዳ የባሕርይ ለውጦችን እንደ መደበት፤ጭንቀት እና የመርሳት ችግር የመሳሰሉትን ሊያስከትል ይችላል፡፡
3) ጉበት
ጉበት የምግብ መፈጨት፤ንጥረ ነገሮችን ማከማቸት፤ኢንፌክሽን የመቆጣጠር እና መርዛማ ነገሮችን ከሰውነት የማስወገድ ተግባርን የሚያከናውን የሰውንት ክፍል ነው፡፡ ታድያ አልኮልን የምናዘወትር ከሆነ በጉበት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እናደርሳለን፡፡
4) ኩላሊት
የአልኮል መጠጥ በብዛት መውሰድ በኩላሊት የሥራ ሂደት ላይ መዛባትን ስለሚፈጥር በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች መመጣጠንን በመረበሽ ጉዳትን ያስከትላል፡፡ይህም ለከፍተኛ የደም ግፊት መጠን መጨመር ይዳርጋል፡፡ ኩላሊትንም ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ እንዲሆን ይዳርጋል፡፡
5) ቆሽት
ልክ እንደ አንጎል ሁሉ ከፍተኛ አልኮልን መውሰድ የቆሽትን ሥራ ያዛባል፡፡ ቆሽት የሚያመነጫቸው ኤንዛየምዎች(Enzymes) በውስጡ እንዲጠራቀም በማድረግ ቆሽት እንዲቆጣ ያደርጋል፡፡ ይህም የሆድ ሕመምን፤ማቅለሽለሽና ማስመለስ፤የልብምት መጨመር ተቅማጥና ትኩሳት ያስከትላል፡፡የቆሽት መቆጣት በሚቆይ ጊዜ የቆሽትን ሥራ ስለሚያስተጓጉል ለስኳር ሕመም አልፎም ለሞት ይዳርጋል፡፡
የአልኮል መጠጥ ማዘውተር ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችም ጉዳቶችን ስለሚያስከትል ለጤንንትዎ ሲሉ እንዲያቆሙ ይመከራል፡፡
ምንጭ – (ዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም)

Advertisement