የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ – How Reduce The Risk of Breast Cancer

                                                   

የጡት ካንሰር በአብዛኛው ሴቶችን የሚያጠቃ የጤና እክል ሲሆን በጊዜ መፍትሄ ካልተሰጠው ከበድ ያለ ጉዳት ያስከትላል።

የህክምና ባለሙያዎችም ይህን በሽታ ለመከላከል መጀመሪያ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል መልካም መሆኑን ይመክራሉ።

አለም አቀፉ የካንሰር ምርምር ፈንድ እና የአሜሪካ ካንሰር ምርምር ተቋም በዘርፉ ላይ የተደረጉ ከ100 በላይ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ለዚህ ይበጃል ያሉትን ግኝት ይፋ አድርገዋል።

በሁለቱ ተቋማት ይፋ የተደረገው የጡት ካንሰር መከላከያ መንገድ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ ሶስት ጉዳዮችን ያካተተ ነው።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ በየዕለቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በተለይም ከጉልምስና በኋላ የሚመጣን የጡት ካንሰርን ለመከላከል ይረዳል ነው የሚለው የሁለቱ ተቋማት የጥናት ሪፖርት።

ሰዎች የሚከተሉት የአኗኗር ዘይቤ ለእያንዳንዱ ነገር የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው በሲያትል የካንሰር ምርምር ማዕከል ተመራማሪዋ ዶክተር ማክቲዬርናን ይናገራሉ።

የመጀመሪያ መፍትሄ የተባለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፥ የልብ በሽታ እና አይነት ሁለት የስኳር በሽታን ስለሚከላከል በእነዚህ አጋጣሚዎች የሚፈጠርን ካንሰር ማስወገድ እንደሚያስችልም ነው ባለሙያዋ የሚናገሩት።

በዚህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሳተፉ ሴቶችም መውለድ ካቆሙ በኋላ የሚከሰት የካንሰር ተጋላጭነታቸውን በ13 በመቶ መቀነስ ይችላሉ።

ለዚህ ደግሞ በቀን ለ30 ደቂቃዎች ያክል የእግር ጉዞ ማድረግና ቤት ውስጥም ሆነ ግቢ ውስጥ መንቀሳቀስን ያካትታል።

ከዚህ ባለፈም በአካል ብቃት እንቅስቃሴ በንቃት የሚሳተፉ ሴቶች በመጠኑ ከሚንቀሳቀሱት በተሻለ በ17 በመቶ ለዚህ ችግር የመጋለጥ እድላቸው የቀነሰ ነው ተብሏል።

መውለድ ያቆሙ ሴቶች ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ቢሰሩ በ10 በመቶ ለዚህ ችግር የመዳረግ እድላቸው ይቀንሳል።

የተስተካከለ አቋም፦ ሴቶች በወጣትነት ዘመናቸው ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት ከተዳረጉ በጎልማሳነት እድሜ ላይ ለዚህ ችግር የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም ዶክተር ማክቲዬርናን ያነሳሉ።

 እንደ እርሳቸው ገለጻ የወጣትነት ዘመናቸውን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ርቀውና ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት ተጋልጠው ያሳለፉ ሴቶች በዚህ እድሜ ክልል ሲደርሱ በዚህ በሽታ ይጠቃሉ።

እናም ሴቶች ሰውነታቸው ከሚሸከመው በላይ በሆነ ውፍረት የሚጋለጡ ከሆነ ለዚህ ችግር ይጋለጣሉና የተስተካከለ አቋም መያዝ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።

አልኮል አለመጠጣት፦ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም መጠነኛ በሚባል መልኩም ቢሆን አልኮል መጎንጨት ለዚህ ችግር ያጋልጣል።

በአነስተኛ ብርጭቆ በቀን አንድ ወይን መጎንጨት በጡት ካንሰር የመያዝ እድልን ከ5 እስክ 9 በመቶ ይጨምራል ይላሉ።

ከዚህ ባለፈም ሲጋራ ማጨስ ለዚህ ችግር ያጋልጣልና ከዚህ ተቆጠቡም ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ።

አመጋገብ፦ የካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሌላው መፍትሄ አመጋገብ መሆኑም በዚህ ጥናት ተዳሷል።

ቢቻል ከላይ የተጠቀሱትን እያደረጉ፥ “ሜዲትራንያን ዳይት” የሚባለውን አመጋገብ መከተል መልካም መሆኑንም ይመክራሉ።

አረንጓዴ የአትክልት ዘሮችን ከአሳ እና ጥራጥሬ ጋር መመገብ፤ ከእርሱ ጋር ይስማማል የሚባለውን የወይን መጠጥ ግን ያስወግዱ።

ምንጭ፦ webmd.com

Advertisement